የአሜሪካ ምጣኔ ሐብት እያሽቆለቆለ መሄድ የኢኮኖሚ ድቀት ስጋት ፈጠረ

ግብይት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የአሜሪካ  ኢኮኖሚ በተከታታይ ለሁለተኛ የሩብ ዓመት አሽቆለቆለ።

እስከ ሐምሌ ባሉ ሦስት ወራት ኢኮኖሚው በዓመታዊ 0.9% ማሽቆልቆሉ ሰፊ ትኩረትን ስቧል።

ይህ በሌሎች አገራት እንደ ኢኮኖሚያዊ ድቀት ተደርጎ ይቆጠራል።

በአሜሪካ ከእአአ 1981 ዓ.ም. ወዲህ የሸቀጣ ሸቀጥ፣ የነዳጅ እና የሌሎች መሠረታዊ ቁሶች ዋጋ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው።

የሕዝብ አመኔታቸው እየቀነሰ የመጣው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢኮኖሚው ጤናማ መሆኑን ለማሳየት የሥራ አጥነት መጠን ከ3.6 በመቶ እንዳልተሻገረ እና ቅጥርም ከፍተኛ ሆኖ መቀጠሉን ገልጸዋል።

"የእኛን የሥራ ዕድል፣ የሸማቾች ወጪን፣ የንግድ ኢንቨስትመንትን ከተመለከትን የኢኮኖሚ መሻሻል ምልክቶችን እናያለን" ሲሉ ባይደን አሜሪካ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች ጠቁመዋል።

በፈረንጆቹ 2022 የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የአሜሪካ ኢኮኖሚ በ1.6 በመቶ ቀንሷል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ማሽቆልቆል ምንያት ነው ሲሉ በወቅቱ ገልጸው ነበር።

ሐሙስ የወጣው ዘገባ ግን ኢኮኖሚው በመኖሪያ ቤት ገበያ፣ በኢንቨስትመንት እና በመንግሥት ወጪ ማሽቆልቆል ይበልጥ መቀዛቀዝ አሳይቷል።

ሰዎች በጤና፣ በመኖሪያ ቤት እና በምግብ ዙሪያ ይበልጥ ወጪ ስለሚያወጡ የሸማቾች ወጪ አንድ በመቶ የሆነ ዓመታዊ እድገት አስመዝግቧል።

የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ጄፍሪ ፍራንኬል ብዙ የሥራ ዕድል በመፈጠሩ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ የኢኮኖሚ ድቀት የጀመረ አይመስለኝም ይላሉ።

"ነገሮች ተቀዛቅዘዋል። ስለዚህ ሁሉም ነገር ጥሩ ነው እያልኩ አይደለም። ወደፊት የኢኮኖሚ ድቀት የማጋጠም ዕድሉ በጣም ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

በሰኔ ወር የአሜሪካ የዋጋ ግሽበት 9.1 በመቶ ደርሷል። ይህም ከአራት አስርት ዓመታት የታየ ​​ፈጣን የዋጋ ንረት ነው።

ረቡዕ ዕለት የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት የወለድ ምጣኔን ከፍ አድርጓል። ይህም በመጋቢት ዋጋ መጨመር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሁለተኛው እርምጃ ነው።

የብድር ወጪዎችን የበለጠ ውድ በማድረግ፣ የፌደራል ግምጃ ቤቱ እንደ ቤት እና መኪና ባሉ ዕቃዎች ላይ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ ተስፋ አድርጓል።

የቅርብ ጊዜ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት የሸማቾች እምነት እየወደቀና የቤቶች ገበያ መቀዛቀዝ እያሳየ ነው።