ትራምፕ ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ወቅት በካቴና እንደማይታሰሩ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ችሎት በመጪው ማክሰኞ መጋቢት 26፣ 2015 ዓ.ም መቀጠሩ ተዘግቧል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከፍሎሪዳ በግል አውሮፕላናቸው ወደ ኒውዮርክ በመብረር ለፌደራል ደኅንነት አካላት እጃቸውን ይሰጣሉ ተብሏል።
ትራምፕ የወሲብ ፊልም ተዋናይት የሆነችውን ስቶርሚ ዳንኤልስን ዝም ለማሰኘት ከፍለዋታል በተባለው 130 ሺህ ዶላር ክፍያ ጋር በተያያዘ ተከሰዋል።
የክሱ ዝርዝር እስካሁን ይፋ ያልሆነ ሲሆን የትራምፕ ጠበቃም ክሱን ገና እንደሚያነቡት አርብ ዕለት ተናግረዋል።
የሕግ አስከባሪ ባለስልጣን ለሲቢኤስ እንደተናገሩት ትራምፕ እጃቸውን ለባለስልጣናት ማክሰኞ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
በዚህም ሂደት በርካታ ምናልባትም በመቶዎች የሚቆጠሩ የደኅንነት አገልግሎት ሰራተኞች ሊሳተፉበት እንደሚችሉ እኚሁ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ባለስልጣን ተናግረዋል።
ትራምፕ ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ወቅት እጃቸው በካቴና እንደማይታሰርም የገለጹት ባለስልጣኑ፣ በተለምዶ በካቴና ማሰር ተግባራዊ የሚሆነው ለደኅንነት አስጊ ናቸው በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ነው ብለዋል።
ትራምፕ የሚቀርቡበት ችሎት በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት 8፡15 ላይ ነው ተብሏል።
የትራምፕ ጠበቃ ጆ ታኮፒና፣ ደንበኛቸው ማክሰኞ “ምናልባት” ፍርድ ቤት ሊቀርቡ እንደሚችሉ ጠቁመው “እርግጠኛ የሆነ ነገር ግን የለም” ሲሉ ለኤቢሲ ተናግረዋል።
“አቃብያነ ሕግ ከዚህ የፍርድ ሂደት የሚችሉትን ታዋቂነት ለመሸመት ይሞክራሉ” ያሉት ጠበቃው፣ “ሆኖም ፕሬዚዳንቱ እጃቸው በካቴና ታስሮ ፍርድ ቤት አይቀርቡም” ብለዋል።
“በፍርድ ቤቱ ዙሪያ ያሉ ህንጻዎች እንደሚዘጉና ችሎቱም ዝግ እንደሚሆን ተረድቻለሁ” ሲሉም ገልጸዋል።
ለችሎቱ የፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ)፣ የኒውዮርክ የፖሊስ ዲፓርትመንት (ኤንዋይፒዲ)፣ የደኅንነት አገልግሎት ሰራተኞች እንዲሁም የፍርድ ቤት ጸጥታ አካላት በመጣመር የሚሰማሩ ይሆናል።
በትራምፕ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጥቃቶችን እንዲሁም በአቃብያነ ሕግ፣ ዳኞች ወይም በዜጎች ላይ ጥቃቶች ሊሰነዘሩ ይችላሉ የሚል ስጋቶች እንዳሉም ምንጮች ለሲቢኤስ ተናግረዋል። የግዛቲቷ አቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤትም ከወዲሁ “በርካታ ማስፈራሪያዎች” እያስተናገደ እንደሆነ ምንጮቹ ተናግረዋል።












