የትግራይ ደቡባዊ ዞን አመራር አባል ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, social Media
በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን የማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሳምሶን ተፈሪ መስከረም 1/2016 ዓ.ም ምሽት መገደላቸውን የዞኑ ጽህፈት ቤት ለቢቢሲ አረጋገጠ።
ህይወታቸው ያለፈው አመራር ለረጅም ዓመታት በክልሉ በተለያዩ የመንግሥት አስተዳደር ስፍራዎች አንዲሁም በፓርቲ ኃላፊነት ማገልገላቸውም ተገልጿል።
አቶ ሳምሶን ይዝናነኑበት ከነበሩበት ስፍራ አንድ ግለሰብ ወደ ውጭ ጠርቷቸው በጥይት ተኩሶ እንደገደላቸው ከስፍራው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የደቡብ ዞን ፖሊስ ጽህፈት ቤት ክትትትል እና ምርመራ እያደረገ ስለመሆኑ ገልጾ ግለሰቡ በቁጥጥር ስለመዋሉ ያለው ነገር የለም።
አስከሬናቸው ለምርመራ መቀለ ወደሚገኘው አይደር ሆስፒታል ተልኮ ምርመራ ከተደረገበት በኋላም በትናንትናው ዕለት ወደ ማይጨው መመለሱን የዞን ጽህፈት ቤት አክሎ ገልጿል።
የቀድሞው የማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሳምሶን ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነበሩ።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ በክልሉ ስርዓተ አልበኝነት እንደሰፈነና የሳቸው አስተዳደር የማያውቃቸው የግል እስር ቤቶች እንዳሉ ገልጸው ኤርትራውያን ስደተኞች ጨምሮ ነዋሪዎች እየታገቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ እንዲከፍሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በከልሉ ያለውን መንግሥታዊ ስልጣን ሙሉ በሙሉ ባለመቆጣጠሩም ችግሩ መባባሱን በዚሁ ወቅት ጠቁመዋል።
በክልሉ የሚገኘው የፖሊስ ኃይል ከባለስልጣናት ይልቅ ለህዝብ እንዲቆም በሚያስችል መልኩ ከላይ እስከታች በአዲስ መልክ መዋቀሩም ተገልጿል።
የጸጥታው ችግር የፖለቲካው ድክመት እንደሆነ የገለጹት አቶ ጌታቸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲዳከም እየሰሩ አሉ ያሏቸውን የተደራጁ ግለሰቦችን ከሰዋል።
“የትግራይ ፍትህ ቢሮ ባደረገው ጥናት መሰረት በትግራይ ውስጥ መንግሥት የማያውቀው እስር ቤቶች አሉም” ሲሉ ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
“በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እያዋልን ሲሆን በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥም በጅምላ ወደ እስር ቤት እናስገባቸዋለን” ብለዋል አቶ ጌታቸው።
በትግራይ ክልል ያለው የጸጥታ እጦት መባሳሱ የተሰማ ሲሆን ከጥቂት ቀናት በፊት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ጽምብላ ወረዳ የ35 ዓመት አርሶ አደር በጸጥታ ኃይሎች ተደብድቦ መመሞቱን ቤተሰቦቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የጸጥታ ኃይሎች አርሶ አደሩን መሳሪያ በመሸጥ ጠርጥረው በቁጥጥር ስር አውለዋል የተባለ ቢሆንም ግለሰቡ መሳሪያ ሽያጭ ውስጥ ስለመሳተፉ ምንም መረጃ እንደሌለም ተናግረዋል።












