ሲቲ ለሃላንድ ረዘም ያለ ውል ማቅረብ አስቧል፤ ማድሪድ ደግሞ ሃሪ ኬንን ማስፈረም ይሻል

ታትሟል

የክረምቱ የዝውውር መስኮት ሊከፈት ተቃርቧል። የትኛው አንጋፋ አሊያም ወጣት ተጫዋች ወደየት ያቀናል የሚለው መነጋገሪያ ሆኗል። እነሆ አበይት ጭምጭምታዎች።

ማንቸስተር ሲቲ ለኖርዌያዊው አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ ዘለግ ያለ ውል በማቅረብ ተቀናቃኞችን ማራቅ ፈልጓል።

የ22 ዓመቱ አጥቂ እንደ ሪያል ማድሪድ ባሉ ኃያላን ክለቦች ዐይን ተጥሎበታል ሲል ቴሌግራፍ ዘግቧል።

ባለፈው ቅዳሜ የኤፍ ኤ ዋንጫ ያነሳው ሲቲ፤ በሚቀጥለው ቅዳሜ በቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ከኢንተር ሚላን ይጫወታል።

በቅርቡ ከካሪም ቤንዜማ የተለያየው ሪያል ማድሪድ የቶተንሃሙን ሃሪ ኬን ማምጣት እንደሚሻ ያስነበበው ሜይል ነው።

ማድሪድ እንግሊዛዊውን የ29 ዓመት አጥቂ ለማስፈረም 100 ሚሊዮን ፓውንድ ሊያቀርብ ይችላል።

በሃሪ ኬን ጉዳይ የማድሪድ ተቀናቃኝ ሆኖ የቀረበው ማንቸስተር ዩናይትድ ሌላኛውን የ24 ዓመቱን እንግሊዛዊ ከቼልሲ ለማስፈረም እየገፋ ነው።

እንግሊዛዊው አማካይ ሜሰን ማውንት በ50 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ዩናይትድ ሊመጣ ቢችልም የኬን ነገር ግን “አጠራጣሪ ነው” ይላል ቴሌግራፍ በዘገባው።

የማንቸስተር ዩናይትዱ የፊት መስመር ተጫዋች ማርከስ ራሽፈርድ በፈረንሳዩ ፒኤስጂ በጥብቅ ቢፈልግም እሱ ግን ኦልድ ትራፈርድ መቆየት እንደሚፈልግ ሰን ፅፏል።

የስፔኑ ኃያል ማድሪድ የቼልሲውን የ23 ዓመት አጥቂ ካይ ሃቨርትዝ ሞቅ ባለ ገንዘብ ሊያስፈርም ነው ሲል የዘገበው የጀርመኑ ቢልድ ጋዜጣ ነው።

ከበርናቤዩ የለቀቀው የ35 ዓመቱ ካሪም ቤንዜማ ወደ ሳዑዲ አቅንቶ ለአል-ኢትሃድ የሁለት ዓመት ውል ሊፈርም እንደሚችል የፈረንሳይ ጋዜጦች እየፃፉ ነው።

አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ ወደ አሜሪካው ሜጀር ሊግ ሶከር ሊያቀና ይችላል እየተባለ ነው።

የ35 ዓመቱ ሜሲ ኢንተር ማያሚ ለተሰኘው ክለብ የሚፈርም ከሆነ ከአፕል እና ከአዲዳስ ጋር ሊፈራረም ይችላል።

እንዲያም ሆኖ ግን የሚያገኘው ገንዘብ ወደ ሳዑዲ አራቢያ ቢያቀና ከሚያገኘው ያነሰ ነው ሲል ጉለም ባላግ ዘግቧል።

ፉት መርካቶ በፈረንሳይኛ ባወጣው ዘገባው የፈረንሳዩ ፒኤስጂ አሠልጣኝ ክሪስቶፍ ጋልቲዬን አሰናብቶ የቀድሞው የባየርን አሠልጣኝ ጁሊያን ናግልስማንን ሊቀጠር ይችላል ብሏል።

በሌሎች የዝውውር ጭምጭምታዎች ቶተንሃም የብሬንትፈርዱን በረኛ ራያ ማስፈረም እንደሚሻ፤ ቼልሲ ደግሞ የስፖርቲንግ ሊዝበኑን አማካይ ማኑዌል ኡጋርቴን ሊያስፈርም እንደተቃረበ እየተሰማ ነው።

ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ ሞሮኳዊው አማካይ ሶፊያን አምራባትን ለማስፈረም ከባርሴሎና ጋር እንደተናነቀ ተደምጧል።

የዩናይትዱ ብራዚላዊ አማካይ ፍሬድ በሚመጣው ክረምት ኦልድ ትራፈርድን ሊለቁ ከሚችሉ ተጫዋቾች መካከል ነው።

አርሰናል ካይሴዶን ሊያስፈርም ቢስማማም ቼልሲ ግን የተሻለ የዝውውር ገንዘብ ሊያቀርብ እንደሚችል ፋብሪዚዮ ሮማኖ ጠቁሟል።

መድፈኞቹ ከካይሴዶ በተጨማሪ የዌስትሃሙን ዴክለን ራይስ ወደ ኤሜሬትስ ለማስመጣት ዕቅድ አላቸው።