ኬንያዊቷ ነርስ በዓለም አቀፍ ውድድር አሸንፋ 250 ሺህ ዶላር ተሸለመች

የፎቶው ባለመብት, @DXBMediaOffice
ኬንያዊቷ ነርስ የዓለም አቀፉን የነርሶች ሽልማት ውድድርን በማሸነፍ 250 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ተበረከተላት።
በሰሜን ኬንያ መርሳቢት በሚገኘው ሆስፒታል የምትሰራው ነርስ ቀበሌ (Qabale) ዱባ ይህን ሽልማት ያሸነፈችው በምትኖርበት ማኅብረሰብ የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ባደረገችው ጥረት ነው።
በዚህ ውድድር ላይ ከ184 አገራት ከ24 ሺህ በላይ ነርሶች ተሳታፊ ሆነው ነበር።
ነርስ ቀበሌ 'ቀበሌ ዱባ ፋውንዴሽን' በሚል መጠሪያ ያቋቋመችው ድርጅት ታዳጊ ሴቶችን ማብቃት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል።
"በድርጅቴ አማካኝነት ልዩ የሆነ ትምህርት ቤት ከፍቻለሁ። ይህ ትምህር ቤት ልጆች እና ወላጆቻቸውን ያስተምራል። እኔ ለተሻለ ነገ ትምህር ቁልፍ ነው ብዬ አምናለሁ" ብላለች በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ዱባይ ውስጥ በተካሄደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ።
ቀበሌ ያሸነፈችው 'ግሎባል ነርሲንግ አዋርድ' የተካሄደው ሐሙስ ግንቦት 04/2014 ዓ.ም. በዓለም የነርሶች ቀን ላይ ነው።
ቀበሌ እአአ 2013 የነርስ ሙያ ትምህርቷን እየተከታተለች ሳለ በኬንያ በተካሄደ የቁንጅና ውድድር ላይ ተሳትፍ፤ 'ሚስ ቱሪዝም ኬንያ 2013' አሸናፊ ሆና ነበር።
በዚህ ውድድር አሸናፊ መሆኗን ተከትሎ ባገኘችው ተሰሚነት የሴቶች እኩልነት እና የትምህርት እድል ላይ ብዙ ሰርታለች።
በቀበሌ ፋውንዴሽን የተመሰረተው ትምህርት ቤት ቀን ላይ ሴት ልጆችን ከሰዓት በኋላ ደግሞ ወላጆቻቸውን ያስተምራል።
ወደ ትምህርት ቤቷ የሚመጡት ጎልማሶች የሚቀስሙት፣ የመጻፍ እና ማንበብ ክህሎትን ብቻ ሳይሆን፤ ሴቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ መሠረታዊ የጤና ትምህርት ይሰጣቸዋል።
ከወሊድ በኋላ ለሴቶች መደረግ ስላለበት እንክብካቤ፣ የሥነ-ተዋልዶ ጤና እና ስለሴቶች እኩልነት ስልጠና ይሰጣቸዋል።
ይህ የቀበሌ ሥራ በአገሯ እና በተቀረው ዓለም እውቅናን አስገኝቶላታል። እአአ 2019 ላይም ሌላ ዓለም አቀፍ ሽልማትን በማግኘት አሸናፊ ነበረች።












