ኢራን ስዊድናዊውን ዶክተር በሞት ለመቅጣት መዘጋጀቷ እንዳሳሰባት ስዊድን ገለጸች

ስዊድናዊው ዶክተር

የፎቶው ባለመብት, CENTER FOR HUMAN RIGHTS IN IRAN

ታትሟል

ኢራንን ሲሰልል ነበር የተባለው የኢራን የዘር ሃረግ ያለው ስዊድናዊ ዶክተር የተላለፈበት የሞት ቅጣት በዚህ ወር እንደሚተገበር መሰማቱ ስዊድንን "እጅግ እንዳስጨነቀ" የአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጹ።

የ50 ዓመቱ የሕክምና ባለሙያ ከ15 ቀናት በኋላ [ግንቦት 13/2014 ዓ. ም] እንደሚገደል ምንጮች ተናግረዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሯ አን ሌንዴ በትዊተር ገጻቸው፣ አገራቸው ስዊድን እና የአውሮፓ ኅብረት የሞት ቅጣቱን እንደሚያወግዙት የገለጹ ሲሆን እንዲለቀቅም ጠይቀዋል።

አሕመድሬዛ ጀላሊ የተባለው የድንገተኛ ሕክምና ባለሙያ የሆነው ግለሰብ እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ወደ ኢራን ለሥራ በተጓዘበት ወቅት ለእስራኤል ይሰልላል በሚል በቁጥጥር ስር ውሏል።

የአገሪቱ አብዮታዊ ፍርድ ቤት በ2017 የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ያልተገባ የፍርድ ሂደት ባሉት ችሎት የሞት ቅጣት በይኖበታል።

ጃሊል "ወንጀሉን" እንዲያም ጫን እንደተደረገበት እና ያ ካልሆነ በስዊድን የሚገኙት ልጆቹ ላይ ጉዳት እንደሚደርስባቸው እንደተናገረ ተገልጿል።

ከአውሮፓ ኅብረት ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ተጠቅሞ ለኢራን እንዲሰልል የተጠየቀው ጃሊል ለኢራን እንዲሰልል ተጠይቆ አሻፈረኝ በማለቱ ለብቻው እንዲታሰር ሳይደረግ እንዳልቀረም ተነግሯል።

በፈረንጆቹ 2020 ግለሰቡ የሞት ቅጣቱ ሊፈጸም እንደሆነ ተነግሮት ነበር። ሆኖም ቅጣቱ ሳይፈጸም ወራት ተቆጥረዋል።

ትላንትና የስዊድን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር መረጃ ካላቸው ሰዎች ሰማሁ ብለው እንደተናሩት ከሆነ የጀሊል የሞት ቅጣት በኢራን የዘመን አቆጣጠር በተያዘው ወር መጨረሻ የሚፈጸም ይሆናል።

የኢራን ፍርድ ቤትም የአገሪቱ ብሔራዊ ሚዲያም ስለ ጉዳዩ ያሉት ነገር የለም።

ይህ የኢራን እርምጃ በስዊድን ፍርድ ቤት በቀድሞ የኢራን የፍርድ ቤት ባለሥልጣን ሃምቢ ኑሪ ላይ ከተላለፈበት ውሳኔ ጋር ግንኙነት እንዳለውም ተገምቷል።

ሃምቢ ኑሪ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 በስቶኮልም አየር ማረፊያ በቁጥጥር ስር ውሏል።

በአውሮፓውያኑ 1988 በኢራን በፖለቲካ እስረኞች ላይ በተፈጸመው የጅምላ ግድያ አለው በተባለው ተሳትፎ ክስ መስርቶበታል።

ሆኖም ተከሳሹ ድርጊቱን ክዶ የተከራከረ ሲሆን የተሳሳተ ሰው ይዛችኋል እንዳለም ተሰምቷል።

የፍርድ ሂደቱ ትላንት የተጠናቀቀ ሲሆን የመጨረሻ ውሳኔ በሃምሌ ወር እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

ግለሰቡ የዕድሜ ልክ እስራት ሊጠብቀው እንደሚችልም ተገምቷል።

ይህ ከተሰማ በኋላ የኢራን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ለስዊዲን አቻቸው ደውለው ሕገ ወጥ ካሉት እስር ኑሪ እንዲፈታ መጠየቃቸውን የኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።