የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝደንት አስክሬን ሽኝት በመዲናዋ እየተከናወነ ነው

የአስክሬን ሽያጭ
ታትሟል

ባሳለፍነው ሳምንት ሕይወታቸው ያለፈው የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ሙዋይ ኪባኪ ይፋዊ የአስክሬን ሽኝት ስነ-ስርዓት ዛሬ አርብ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ እየተካሄደ ነው።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የጎረቤት አገራት መሪዎችና ሌሎች ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

በርካታ ኬንያውያንም በመዲናዋ በሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም በመገኘት የቀድሞ ፕሬዝዳንታቸውን እየተሰናበቱ ነው።

በቀድሞው ፕሬዝዳንት የአስክሬን የሽኝት ስነ-ስርዓት ላይ ለመገኘት ኬንያ ከገቡት መካከል የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ፣ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና የደቡብ ሱዳኑ መሪ ሳልቭ ኪር ይገኙበታል።

የኬንያ ሪፐብሊክ ሦስተኛው ፕሬዝደንት የነበሩት ሙዋይ ኪባኪ የምስራቅ አፍሪካዊቷን አገር ከእ.አ.አ. 2002 እስከ 2012 ድረስ መርተዋል።

የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ የቀድሞ ፕሬዝደንቱ ሥርዓተ ቀብር እስኪፈጸም ድረስ ብሔራዊ ሐዘን አውጀው የነበረ ሲሆን፣ የቀብር ስርዓታቸው እስኪፈጸም ድረስ የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማም ዝቅ ብሎ እየተውለበለበ ይገኛል።

በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓመት በሞት የተለዩት ሙዋይ ኪባኪ ኬንያ ውስጥ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን፣ አዲስ ሕገ መንግሥት፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና ትምህርት ዘርፎች ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

በስልጣን ዘመናቸው ኬንያ በሙስና ተዘፍቃ የነበረች ሲሆን ስልጣን ላይ እስከነበሩበት ጊዜ ድረስ የሙስና ወንጀልን ለመዋጋት ከፍተኛ ጥረቶችን አድርገዋል።

ለሁለተኛ ጊዜ የኬንያ ፕሬዝደንት ሆነው ሲመረጡ ደግሞ ከፍተኛ አመጽ ተከስቶ ነበር። የወቅቱ ተቀናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋ በአውሮፓውያኑ 2007 የተካሄደውን ብሄራዊ ምርጫ ውጤት አልቀበልም ማለታቸው የሚታወስ ነው። ይህንን ተከትሎም በአገሪቱ ከፍተኛ አለመረጋጋት ተከስቶ ነበር።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት በገጠሪቱ የኬንያ ክፍል በሚገኘው የትውልድ መንደራቸው ነገ ቅዳሜ ቀብራቸው ይፈጸማል።

በናይሮቢ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የሽኝት ስነ-ስርዓት በንያዮ ብሔራዊ ስታዲየም ሲሆን ይህንን ተከትሎም የናይሮቢ ዋና ዋና ጎዳናዎች እንግዶችን ለማስተናገድ በሚል ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ ተገልጿል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ኬንያውያን ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ያለቸውን ፍቅርና ክብር ሲገልጹ ቆይተዋል።

ጎረቤት አገር ታንዛኒያ ደግሞ የቀድሞው ፕሬዝዳንትን ሞት ተከትሎ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሀዘን አውጃለች።