የሩሲያን ወረራ መገመት አልቻሉም የተባሉት የፈረንሳይ የስለላ ኃላፊ ከሥራ ተባረሩ

ታትሟል

የሩሲያን እና የዩክሬን ጦርነትን መተንበይ አልቻሉም የተባሉት የፈረንሳይ ወታደራዊ ስለላ ኃላፊ ጄኔራል ኤሪክ ቪዱ ከሥራ ሊሰናበቱ መሆኑን ሪፖርቶች አመልክተዋል።

ከተሾሙ ሰባት ወር የሆናቸው ኃላፊው "በቂ ያልሆነ ማብራሪያ የመስጠት" እና "ጉዳዮችን የማየት ችሎታ ማነስ" ታይቶባቸዋል የሚል ቅሬታ እንደቀረበባቸው አንድ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

ከሩሲያ ዩክሬን ወረራ በፊት አሜሪካ ሞስኮ መጠነ ሰፊ ወረራ ለማድረግ እያቀደች ነው ስትል ፈረንሳይ በበኩሏ ይህ የማይመስል ነገር ነው ብላ ነበር።

የፈረንሳይ የጦር አዛዥ ለዚህ ተጠያቂ ያደረጉት ጄኔራል ቪዱን መሆኑን ተዘግቧል።

ወታደራዊ ምንጭ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደገለጸው ግን የዚህ ኃላፊ ሥራ "ስለዘመቻዎች ወታደራዊ ስለላ መስጠት እንጂ በቅድመ ዝግጅት ላይ አይደለም" ብሏል።

የጄኔራል ቪዱ ቢሮ ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር የሚያስችል አቅም እንዳላት መደምደሙ "የተፈጠረው ነገር ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል" ብሏል ይህ ምንጭ።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከፈረንሳይ ጦር መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የጦሩ ቃል አቀባይ ጄነራል ቲዬሪ ቡካር በመጋቢት ወር የፈረንሳይ የስለላ ድርጅት መረጃ ከአሜሪካ እና ዩናትድ ኪንግደም ጋር የሚስተካከል አልነበረም።

"ሩሲያውያን ጥቃት ሊሰነዝሩ ነው ብለው አሜሪካዊያን ሲገልጹ ልክ ነበሩ" ሲሉ ለ ሞንድ ጋዜጣ ተናግረዋል።

የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪን ከስልጣን ለማውረድ "ዩክሬንን መውረር ወጪው እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ሩሲያውያን ሌላ አማራጭ አላቸው" ሲል የስልላ ድርጅታችን አስታውቆ ነበር ብለዋል።

ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን ወረራው ከመጀመሩ እስከ ጥቂት ቀናት ድረስ በተደጋጋሚ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ውይይት እያደረጉም ነው ፈረንሳይ በጉዳዩ ላይ የተሳሰተ ግምት የወሰደችው።

የስለላ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር አሌክሳንደር ፓፓኤማኑኤል ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት ለስህተቱ ወታደራዊው የስለላ ክፍል ተጠያቂ ማድረግ በጣም ቀላል ቢሆንም ይህ ግን የሁሉም የፈረንሳይ የስለላ ማህበረሰብ ጉዳይ ነው።

የፈረንሳይ የቀድሞ የልዩ ኃይል አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ቪዱ በሌሎች ምክንያቶችም ጫና ውስጥ የገቡ ይመስላል።

የጦሩን የስለላ ኃላፊነት ከያዙ ከሳምንታት በኋላ አውስትራሊያ ከፈረንሳይ ጋር የነበራት የባለብዙ ዶላር የባህር ሰርጓጅ መርከብ ውል በመሰረዝ ከአሜሪካ እና እንግሊዝ ጋር መስማማቷ ትችት ፈጥሮባቸዋል።