ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኡጋንዳ በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸውን የመረጃና ደህንነት ኃላፊን ከስልጣን አነሳች
ታትሟል
በኡጋንዳ ጦር የመረጃና ደኅንነት ኃላፊ የሆኑት ሜጀር ጄኔራል አቤል ካንዲሆ ላይ አሜሪካ በሰብአዊ መብት ረገጣ ምክንያት ማዕቀብ መጣሏን ተከትሎ ከስልጣናቸው እንዲነሱ ተደረጉ።
ኃላፊው በአሜሪካ በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ላይ ማዕቀብ የተጣለባቸው ከሳምንታት በፊት ነው።
የጦሩ የመረጃና ደኅንነት ኃላፊነትንም ሜጀር ጄኔራል ጄምስ ቢሩንጊ ተረክበዋል።
ከኃላፊነት የተነሱት ሜጀር ጄኔራል አቤል ካንዲሆ የደህንነት ክትትል ሜካኒዝምን እንዲመሩ ወደ ደቡብ ሱዳን ተልከዋል ሲል የኡጋንዳ ጦር መግለጫ አትቷል።
የሜጀር ጄነራሉ ዝውውሩ የፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ ሌተናል ጄኔራል ካይኔሩጋባ ሙሆዚ ሩዋንዳን ጎብኝተው ከፕሬዚዳንት ፖል ካጋሙ ጋር ከተነጋገሩ ከቀናት በኋላ ነው።
ለአመታት ያህል በውጥረት ላይ በነበሩት ሁለት አገራት የካይኔሩጋባ ጉብኝት አዲስ ምዕራፍ ሰንቋል ተብሏል።
ሩዋንዳ ቀደም ሲል ሜጀር ጄኔራል ካንዲሆ ከሩዋንዳ ተቃዋሚዎች ጋር ይተባበራል በማለት ሰትከስ ነበር።
የሜጄር ጀነራል ካንዲሆ ምክትል የአገሪቱን ጸረ-ሙስና ክፍልን እንዲመሩ በድጋሚ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።