በኬንያ ወንዝ ውስጥ አስክሬኖች መገኘታቸው ቁጣን ቀሰቀሰ

አስከሬኖች የተገኙበት ያላ ወንዝ

የፎቶው ባለመብት, @bonifacemwangi

የምስሉ መግለጫ, አስከሬኖች የተገኙበት ያላ ወንዝ
ታትሟል

በአገረ ኬንያ የበርካታ ሰዎች አስክሬን ለተከታታይ ሳምንታት ከአንድ ወንዝ ውስጥ መገኘቱ ቁጣን ቀሰቀሰ።

ሃኪ አፍሪካ የተሰኘ የሰብዓዊ መብት ተቋም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ቢያንስ 20 አስክሬኖች በምዕራባዊ ኬንያ ከሚገኝ ወንዝ ውስጥ መውጣታቸውን አስታውቋል።

ሃኪ አፍሪካ ለቢቢሲ እንደገለጸው ወደ ቪክቶሪያ ሀይቅ ከሚፈሰው ያላ ወንዝ እየወጡ ያሉት አብዛኛዎቹ አስክሬኖች በጆንያ የተጠቀለሉ ሲሆኑ የተወሰኑት አካላቸው የተቆራረጡ ናቸው።

እስካሁን ድረስ የሟቾቹ ማንነትም አልታወቀም፤ ለወንጀሉ ተጠያቂ የሆነ አካልም አልተገኘም።

የሃኪ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ሁሴን ካሊድ እንደገለጹት በአካባቢው ያለው የሬሳ ማቆያ ማንነታቸው ያልታወቁ አስክሬኖች እየተቀበለ ሲሆን፤ ለተጨማሪ አስክሬኖች ቦታ ለመተው ዘጠኙን አስክሬኖች በጅምላ ለመቅበር ተገደዋል።

አስክሬኖቹ ሌሊት ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ወደ ወንዙ እንደሚጣሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የመብት ተሟጋቹ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ሁሴን ካሊድ እና የተቃዋሚ ፓርቲ አባል እና የማህብረሰብ አንቂ የሆነው ቦኒፌስ ምዋንጊ ወደ ስፍራው ከተጓዙ በኋላ ሁለት ተጨማሪ አስክሬኖች በወንዙ ላይ ሲንሳፈፉ ማየታቸውን ተናግረዋል።

ምዋንጊ በትዊተር ገጹ ላይ አስክሬኖቹ የተገኙበትን አካባቢ በምስል አጋርቷል።

የኬንያ ፖሊስ በአሁኑ ወቅት በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል እየተከሰተ ያለው ክስተት ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ የነበረ እንደሆነ ገልጿል።

የፖሊስ ቃል አቀባይ ብሩኖ ሺኦሶ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እስካሁን እየተደረገ ባለው ምርመራ የግድያውን መንስኤ ለመለየት አልተቻለም።

የቢቢሲው ፈርዲናንድ ኦሞንዲ ከኪሱሙ እንደዘገበው ከያላ ወንዝ ዳርቻ የወጡ 20 አስክሬኖች በያላ ሰብ ካውንቲ ሆስፒታል የሚገኙ ሲሆን እስካሁን ቤተሰባቸውን ወይም ማንነታቸውን የሚያውቅ አልተገኘም።

ፖሊስ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ምን ያህል አስክሬን እንደተገኘ ማወቅ እንደማይችል የተናገረ ሲሆን፤ የያላ ሆስፒታል አስተዳዳሪ በበኩላቸው በማቆያቸው ውስጥ ያሉ ጠያቂ የሌላቸው አስክሬኖች በየ90 ቀኑ ይቀበራሉ ብለዋል።

ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ አስክሬኑን ለማውጣት እገዛ እያደረገ መሆኑን የሚናገረው አንድ የውሃ ጠላቂ ዋናተኛ በበኩሉ በወንዙ ውስጥ ብዙ የበሰበሱ ሌሎች አስክሬኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያምናል።

ታዲያ ይህንኑ ውሃ ነው የአካባቢው ነዋሪዎች ለቤት ውስጥ ፍጆታ የሚጠቀሙት።

የአካባቢ ነዋሪዎች እንደሚሉት አብዛኞቹ አስክሬኖች የስቅይ ምልክት ታይቶባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል። በክስተቱ የተደናገጡ በርካታ ኬንያውያን መልስ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ ነው።