የአፍሪካ ዋንጫ የአራት ጊዜ አሸናፊዋ ጋና ከምድቧ ሳታልፍ ቀረች

ትላንት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ ኮሞሮስን የገጠመችው ጋና ሁለት ለሦስት ተሸንፋ ከ2022 የአፋሪካ ዋንጫ መሰናበቷ እርግጥ ሆኗል።
ታትሟል

ትላንት በአፍሪካ ዋንጫ የመጨሻ የምድብ ጨዋታዋን ከኮሞሮስ ጋር ያደረገችው ጋና ሁለት ለሦስት ተሸንፋ ከ2022 የአፋሪካ ዋንጫ መሰናበቷ እርግጥ ሆኗል።

የአፍሪካ ዋንጫ የአራት ጊዜ ባለ ድል ጋና በመጀመርያው ዙር በእግር ኳስ እምብዛም በማትታወቀው ኮሞሮስ አሳፋሪ የተባለ ሽንፈትን ነው ያስተናገደችው።

የኮሞሮሱ ኤል ፋርዱ ቤን ናቦውሃኔ ያስቆጠራት ጎል የደሴቷን አገር በጨዋታውን እንድትመራ አድርጓታል። የክንፍ ተጫዋቿ አንድሬ አየው በቀጥታ ቀይ ካርድ የተሰናበተባት ጋና ጨዋታውን በአስር ሰው ለማካሄድ ተገዳለች።

ጥቋቁር ከዋክብት የሚሰኘው የጋና ብሔራዊ ቡድን በጨዋታው ከተቆጠረባቸው ግብ በኋላ ሁለት አቻ ላይ መድረስ ችለው ነበር።

ሆኖም መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃ ሲቀር ሞግኒ ለኮሞሮስ ሦስተኛውን ግብ አስቆጥሯል።

ሽንፈቱ እንደ አውሮፓውያኑ ከ2006 በኋላ የጋና ብሔራዊ ቡድን በጊዜ ከውድድሩ የተሸኘበት ሆኖ ተመዝግቧል።

ጋና እና ኮሞሮስ በተካተቱበት ሦስተኛው ምድብ ኮሞሮስ በውድድሩ የመጀመሪያ ድሏን አስመዝግባ ምርጥ ሶስተኛ ሆና ወደ ጥሎ ማለፍ የመሸጋገር እድል አላት ተብሏል።

የኮሞሮስ ብሔራዊ ቡድን በዓለም የእግር ኳስ ደረጃ 132ኛ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ከጋና ብሔራዊ ቡድን ቁልቁል ርቆ የሚገኝ ነው።

ምንም እንኳን ቡድኑ በዘንድሮ ውድድር የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጨዋታዎች በሽንፈት ቢያጠናቅቅም በትላንቱ ድሉ ግን ምርጥ ሦስተኛ በመሆን ወደ ጥሎ የማለፍ ዕድል ሊያገኝ ይችላል።

ከአንድ ሚሊዮን በታች ሕዝብ ያላት ትንሿ ደሴት አገር ኮሞሮስ እንደ አውሮፓውያኑ በ1996 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባጋጠው አደጋ ብዙዎች ያውቋታል።

የተቀረው ዓለም ደግሞ በመፈንቅለ መንግሥት ታሪኳ የሚያነሳት ሲሆን በእግር ኳሷ እምብዛም የምትታወቅ አይመስልም።

ትላንት በ2022 አፍሪካ ዋንጫ የውድድሩን የአራት ጊዜ ባለ ድል ጋናን ያሸነፈችበት ጨዋታ በእግር ኳስ ታሪኳ ትልቅ ክስተት ሆኖ ተመዝግቦላታል።