ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና 'ወኪሏን' ወደ ዩኬ ፓርላማ አስገብታለች መባሉን አስተባበለች
የዩናይትድ ኪንግደም የደህንነት ተቋም (ኤምአይ5) ቻይና ወኪሏን የዩኬ ፓርላማ ውስጥ አስርጋ አስገብታለች ማለቱን ተከትሎ ቤይጂንግ ክሱን አጣጣለች።
የደህንነት መስሪያ ቤቱ እንዳለው ክሪስቲን ቺንግ ኩይ የፓርላማ አባላት እና በቀጣይ አባል ለመሆን የሚፈልጉ ግለሰቦች ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጋር "ግንኙነት እንዲመሠርቱ" አግዛለች ብሏል።
ከ420,000 ፓውንድ በላይ ከግለሰቧ ድጋፍ የተደረገለት የሌበር ፓርቲ ተወካዩ ባሪ ጋርዲነርን ጨምሮ ለሌሎች ፖለቲከኞችም ድጋፍ አድርጋለች።
መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የቻይና ኤምባሲ ኤምአይ5 በእንግሊዝ በሚገኙ የቻይና ማህበረሰብ አባላትን 'ስም እያጠፋ እና እያስፈራራ ነው' ሲል ከሷል።
የኤምባሲው ቃል አቀባይ በኤምባሲው ድረ-ገጽ ላይ በሰጡት መግለጫ "ቻይና በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የሚለውን መርህ ሁሌም ትከተላለች" ብለዋል።
"በማንኛውም አገር ፓርላማ ውስጥ 'ተጽዕኖ ለመፍጠር' ምንም ፍላጎት የለንም። በእንግሊዝ የቻይና ማህበረሰብ አባላት ላይ የሚደረገውን ስም ማጥፋት እና ማስፈራራት አጥብቀን እንቃወማለን" ብሏል።
እንደ ኤምአይ5 ማስጠንቀቂያው ከሆነ ሊ ከፓርላማው ጋር የነበራት ግንኙነት "እንግሊዛዊ የሆኑ ቻይና ዝርያ ያላቸውን ለመወከል እና ብዝሃነትን ለማሳደግ" ነበር።
ኤምአይ5 በኩሉ እንቅስቃሴው "ከዩናይትድ ፍሮንት ዎርክ ዲፓርትመንት (የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አካል ነው) ጋር በድብቅ መካሄዱን አሰስታውቆ የገንዘብ ድጋፍ በቻይና እና ሆንግ ኮንግ በሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች ተደርጓል" ብሏል።
ዲፓርተመንቱ የዩናይትድ ኪንግደም የፖለቲካ ምህዳር ለኮሚኒስት ፓርቲው ምቹ መሆኑን ለማረጋገጥ እና የሰብዓዊ መብቶችን ጨምሮ በፓርቲው ላይ ስጋቶችን የሚያነሱትን ለመቃወም "ከተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች" ጋር "ግንኙነትን ለማዳበር" ያለመ ነው ተብሏል።
የደህንነት ቢሮው እንዳለው ግለሰቧ ቻይናዊያን በብሪታንያ ተብሎ የሚጠራውንና አሁን የተበተነውን ኦል ፓርቲ ፓርላመንተሪ ግሩፕን ጨምሮ "በዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲካ ውስጥ ካሉ ግለሰቦች ጋር ሰፊ ግንኙነት ነበራት" ብሏል።
ኤምአይ5 አክሎም "የቻይናን የኮሚኒስት ፓርቲን አጀንዳ ለማራመድ የፓርላማ ቡድኖችን ለማቋቋም ልትፈልግ ትችላለች" በማለት አስጠንቅቋል።
ወግ አጥባቂ የህዝብ እንደራሴ እና የቀድሞ የፓርቲ ሊቀመንበር ሰር ኢይን ደንካን ስሚዝ ሐሙስ በፓርላማው ስለማስጠንቀቂያው ያነሱ ሲሆን ይህም በአፈ ጉባኤው ለፓርላማ አባላት እንደተላከ አረጋግጠዋል።
"በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው" ያሉ ሲሆን ሊ ከሃገራቸው እንድትባረር እና መንግሥት ለምክር ቤቱ መግለጫ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴል "የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲን ወክላ በፖለቲካ ጣልቃገብነት ተግባር ላይ የተሠማራች ግለሰብ የፓርላማ አባላት ላይ ማነጣጠሯ በጣም አሳሳቢ ነው" ብለዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም "የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመለየት" እርምጃዎች እንዳሏት ተናግረዋል።
የሌበር ፓርቲ የህዝብ እንደራሴ ባሪ ጋርዲነር ከክርስቲን ቺንግ ኩይ ሊ የህግ ቢሮ ድጋፍ ማግኘት የጀመሩት እአአ ከ2014 ጀምሮ ነው።
የሊ ልጅ ለህዝብ እንደራሴው በበጎ ፈቃደኝነት መሥራቱን እና በኋላም ቃለ ጉባኤ ያዥ ሆኖ ተቀጠሯል።
ዠርሚ ኮርቢ የሌበር መሪ በነበሩበት ጊዜ የትይዩ ካቢኔ አባል የነበሩት ጋርዲነር ስለግለሰቧ "ለተወሰኑ ዓመታት ከደህንነት አገልግሎታችን ጋር ግንኙነት ሳደርግ ነበር" ብለዋል።
ሊ የጥናት ባለሙያ ሆኖ በተሾመበት ወቅት ምንም ሚና ያልነበራት ሲሆን ሁሉም ልገሳዎችም "በትክክል ሪፖርት የተደረጉ ናቸው" ብለዋል።
ጋርዲነር በኋላ ላይ ለስካይ ኒውስ "በእኔ እይታ ገንዘቡ በፓርላማ ውስጥ መሥራት የቻልኩትን ሥራ ለማሻሻል እና ለምርጫ ክልሌ ልሠራው የቻልኩትን ለማሻሻል የዋለ ነበር። ለግል ጥቅሜ የዋለ ገንዘብ የለም" ብለዋል።