ተቃውሞ ተጠናክሮ በቀጠለባት አውሮፓ፤ ኦስትሪያ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች

አድማ በተኝ ፖሊስ በቤልጂየም ብራሰልስ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, አድማ በተኝ ፖሊስ በቤልጂየም ብራሰልስ
ታትሟል

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት አዲስ የወጡ የእንቅስቃሴ ገደቦች አውሮፓ ተቃውሞ እየገጠማቸው ባለበት ወቅት አውሮፓዊቷ ኦስትሪያ አዲስ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላለች።

ከትላንት ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ ኦስትሪያውያን ከቤት እንዲሠሩ የታዘዙ ሲሆን መሠረታዊ አገለግሎት የማይሰጡ የንግድ ተቋማትም ተዘግተዋል።

የተለያዩ የአውሮፓ አገራት እንደ አዲስ የእንቅስቃሴ እገዳዎችን የጣሉ ሲሆን ይህም ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠመው ነው።

የእንቅስቃሴ ገደቡን በመቀወም በኔዘርላንድስ፣ ቤልጂየም፣ ክሮሺያ እና ዴንማርክ ሰዎች ድምጻቸው አሰምተዋል።

በኔዘርላንድስ እና ቤልጂየም ደግሞ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።

በአህጉሪቱ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ቅዳሜ ዕለት በአውሮፓ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ሃንስ ክሉጅ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በመላው አውሮፓ እንደ ክትባት መውሰድን እና የፊት እና አፍ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግን የመሰሉ እርምጃዎች በጥብቅ ካልተተገበሩ፤ በሚቀጥለው የፀደይ ወራት በቫይረሱ ምክንያት ግማሽ ሚሊዮን ተጨማሪ ሞት ሊመዘገብ ይችላል።

ባለፈው ሳምንት ኦስትሪያ የኮቪድ-19 ክትባትን መውሰድ ሕጋዊ ግዴታ ያደረገች የመጀመሪያዋ አውሮፓ አገር ሆናለች።

ሕጉ በየካቲት ወር ተግባራዊ ይሆናል። በአጎራባቿ ጀርመን ያሉ ፖለቲከኞች ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እየመከሩ ነው ተብሏል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ኦስትሪያ ለአራተኛው ጊዜ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላለች።

የአገሪቱ ባለስልጣናት ምግብ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ ፀጉር ቤቶች፣ ቲያትር ቤቶች እና መሠረታዊ አገልግሎት የማይሰጡ የንግድ ተቋማት እንዲዘጉ አዘዋል።

የአገሪቱ ጤና ሚንስትር ዎልፍጋንድ ሙቸክስታይን፤ "ከባድ የሆነውን የእንቅስቃሴ ገደብ መጣል ብቸኛው አማራጭ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በኦስትሪያ መዲና ቪዬና የእንቅስቃሴ ገደብ ከመተግበሩ በፊት አደባባይ ወጥተው የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በተለያዩ የአውሮፓ አገራት በሳምንቱ መጨረሻ ኮቪድ-19 ለመከላከል የወጡ እና ጠንከር ያሉ ገደቦችን በመቃወም በርካቶች አደባይ የወጡ ሲሆን አንድ አንድ አገራት ላይ ተቃውሞው ወደ ሁከት ተቀይሮ ታይቷል።