በአሜሪካ አንድ መኪና የተሰበሰቡ ሰዎችን ገጭቶ አምስት ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, CITY OF WAUKESHA/FACEBOOK VIA REUTERS
በአሜሪካዋ ዊስኮንሲን ግዛት አንድ መኪና የተሰበሰቡ ሰዎችን ግጭቶ አምስት ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
በይነ መረብ ላይ የወጡ ምስሎች እንደሚያሳዩት ባለ አራት ጎማ ቀይ መኪና የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ አደባባይ የወጡት ሰዎች ላይ በፍጥነት በመሄድ ጉዳት አድርሷል።
ይህ የሆነው በዊስኮንሲን ግዛት ዉኬሻ በተሰኘችው ከተማ እሁድ ከቀኑ 10፡40 ገደማ ነው።
የፖሊስ መኪና ሕፃናት ጨምሮ ቢያንስ 40 ሰዎችን እንደገጨ አስታውቋል።
ጉዳት ያደረሰው ተጠርጣሪ ከሌላ የወንጀል ድርጊት ለማምለጥ በፍጥነት እያሽከረከረ ሳለ ሰዎችን ገጭቶ ጉዳት ማድረሱ ተዘግቧል።
ይህ ድርጊት እስካሁን ከሽብርተኝነት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ተብሏል።
ፖሊስ በአደጋው ሰዎች መሞታቸውን አስታውቆ ቤተሰቦች መርዶ እስኪነገራቸው ድረስ የሟቾቹን ማንነት እና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የአካባቢው ነዋሪ የሆነው አንጀሊቶ ቴኖሪዮ ሚልዌኪ ጆርናል ሴንቲነል ለተሰኘው ጋዜጣ ሲናገር የገና በዓልን በማስመልከት የተዘጋጀውን ሰልፍ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው መኪናው በፍጥነት ወደ ተሰበሰቡ ሰዎች መካከል የገባው።
"መኪናውን አየን. . . በመሉ ፍጥነት ነበር እየገሰገሰ የመጣው። ከዚያ የሆነ ነገር ሲጋጭ ሰማን። ቀጥሎ በሥፍራው ለቅሶና ጩኸት በረከተ።"
የፖሊስ አዛዥ ቶምፕሰን እንደሚሉት አደጋውን አድርሷል ተብሎ የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
አዛዡ ከኤፍቢአይ ጋር ምርመራ መጀመሩን ተናግረው፤ በቁጥጥር ሥር ስለዋለው ግለሰብ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ቶምፕሰን እንደሚሉት ፖሊስ መኪናው ሰዎችን እየጨፈላለቀ ሲሄድ ለማስቆም ጥይት ተኩሷል።
የእሣት አደጋ ኃላፊው ስቲቨን ሐዋርድ በበኩላቸው ቢያንስ 12 አዋቂ ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የከተማዋ ከንቲባ ሾን ራይሊ ከተማዋ "ከባድ" ጊዜ ላይ ናት ብለው ለአደጋው ተጋላጮች "እየፀለዩ" እንደሆነ ተናግረዋል።
ማኅበራዊ ድር አምባ ላይ የተሰቀለ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው መኪናውን በመንገዱ የነበሩትን ሁሉ እየገጨ ወደ ሰዎች ሲገሰግስ ነበር። በሌላ ምስል ደግሞ መኪናው ተሰባስበው የቆሙ ሙዚቀኞች መሃል ሲገባ ያሳያል።
ዋይት ሐውስ "ጉዳዩን እየተከታተለው ነው" ሲሉ አንድ ባለሥልጣን ተናግረዋል። ፕሬዝደንት ባይደን ስለአደጋው ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ታውቋል።












