ባርሴሎና አሰልጣኝ ሮናልድ ኩማንን አሰናበተ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሮናልድ ኩማን በኑካምፕ ለ14 ወራት ከዘለቀው የባርሴሎና ዋና አሰልጣኝ ሥራቸው ተባረዋል።
ባርሳ በላሊጋው ካደረጋቸው 10 ጨዋታዎች 15 ነጥቦችን ብቻ ሰብስቧል። በዘንድሮው የቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታዎችም ሁለት ጊዜ ተሸንፏል።
ረቡዕ በራዮ ቫሌካኖ ከተሸነፉ በኋላ ከመሪዎቹ በስድስት ነጥብ ርቀው በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ለባርሳ ሽንፈቱ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሦስተኛው ነው። ባለፈው እሁድ በኤል ክላሲኮ በሪያል ማድሪድ መሸነፋቸው ይታወሳል።
የስፔኑ ክለብ ባወጣው መግለጫ "የክለቡ ፕሬዝዳንት ጆአን ላፖርታ ከራዮ ቫሌካኖ ሽንፈት በኋላ ስለ ውሳኔው ለኩማን አሳውቀውታል" ብሏል።
"ሮናልድ ኩማን ሐሙስ ዕለት ቡድኑን ይሰናበታሉ።"
የ58 አመቱ የቀድሞ የኔዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን፣ የኤቨርተን እና የሳውዝሃምፕተን አሰልጣኝ የአምስት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮናዎቹን ባለፈው የውድድር ዓመት በሊጉ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው እንዲጨርሱ አድረጓል።
ክለቡ ያጋጠመው ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ሆላንዳዊውን አልረዳውም። በዚህ ምክንያት ሊዮኔል ሜሲ ወደ ፓሪስ ሴንት ዠርሜይን እንዲዘዋወር ሆኗል።
በክረምቱ ባርሴሎና ለአዳዲስ ፈራሚዎች ምንም ገንዘብ ማውጣትም አልቻለም። ሜምፊስ ዴፓይ፣ ሰርጂዮ አጉዌሮ እና ኤሪክ ጋርሲያ በነጻ ዝውውር ኑ ካመፕ ደርሰዋል። አጥቂው ሉክ ዴ ዮንግ ከሲቪያ በውሰት ተቀላቅሏል።
ከረቡዕ ሽንፈት በኋላ ኩማን "[የባርሴሎና ሊግ አቋም] ደህና አለመሆኑን ያሳያል" ብሏል።
"ይህ የሚያሳየው ቡድኑ ሚዛኑን አጥቷል፣ በጣም ውጤታማ የሆኑ ተጫዋቾችን አጥቷል። ሌላው የሚያሳየው ደግሞ በቅርብ ዓመታት ሌሎች ክለቦች ሲጠናከሩ እኛ ይህን አላደረግንም።"
የኳታሩ ክለብ አል ሳድ አሰልጣኝ የሆነው የቀድሞ የባርሳ አማካይ ዣቪ ኩማንን ለመተካት ከተመረጡት አንዱ ነው።
ከእአአ 1987 ወዲህ ባርሳ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ ጎል ሳያስቆጥር ሲሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ኩማን በመጀመሪያው የውድድር ዘመን የኮፓ ዴልሬይ ዋንጫን ቢያሸንፍም ባርሳ በአትሌቲኮ ማድሪድ እና ሪያል ማድሪድ በላሊጋው ከመበለጡም በላይ ከ2008 በኋላ ዝቅተኛውን ነጥብ ሰብስቦ አጠናቋል።
የቀድሞው የኔዘርላንድ የመሃል ተከላካይ እአአ ከ1989 እስ 1995 ለስፔኑ ክለብ ተጫውቶ አራት የሊግ ዋንጫዎችን አንስቷል።
በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ማሪያ ባርቶሜው ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ወደ ክለቡ እአአ ነሐሴ 2020 ተመልሷል።
አዲሱ ፕሬዝዳንት ላፖርታ ግን የሆላንዳዊው ሹመቱ የሳቸው ውሳኔ አለመሆኑን ደጋግሞ ተናግረዋል።
ግንኙነታቸው መሰናክል የበዛበት ሲሆን ኩማን ሜሲ እና አንቶንዮ ግሪዝማን ካጣ በኋላ እንደገና ቡድኑን ለመገንባት ጊዜ እንዲሰጠው በመጠየቅ መስከረም ላይ መግለጫ አውጥቷል።
ከእሁዱ የማድሪድ ሽንፈት በኋላ የኩማን መኪና በአንዳንድ የባርሴሎና ደጋፊዎች ተከቦ የነበረ ሲሆን አሰልጣኙ በኋላም "ያልተማሩ ሰዎች" ሲል አጣጥሏቸዋል።
ወደ ራዮ ቫሌካኖ ከማቅናታቸው በፊትም "ማህበራዊ ችግር ነው። ደንቦችን እና እሴቶችን ያልተረዱ ያልተማሩ ሰዎች" ሲል ተናግሯል።












