አንዲት ሴት ስትደፈር አይተው ሪፖርት ያላደረጉ መንገደኞች ላይከሰሱ እንደሚችሉ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, NURPHOTO VIA GETTY IMAGES
አሜሪካ፣ ፊላዴልፊያ ውስጥ አንዲት ሴት ስትደፈር አይተው ለፖሊስ ሪፖርት ያላደረጉ ሰዎች የወንጀል ክስ ሊመሠረትባቸው እንደማይችል ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።
የደኅንነት ካሜራዎች እንደሚያሳዩት፤ ይህች ሴት ባቡር ውስጥ ስትደፈር በአቅራቢያዋ የነበሩ መንገደኞች ሴቲቷን ለመርዳት አንዳንችም እርምጃ አልወሰዱም።
ድርጊቱን በካሜራ የቀረጹ ሰዎች ሊከሰሱ እንደሚችሉ ፖሊስ ገልጾ ነበር።
የፔንስልቬንያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በሆነ ባቡር ውስጥ ይህች ሴት የተደፈረችው ባለፈው ረቡዕ ነው።
የባቡር ጣቢያው "ይህ አስጸያፊ ድርጊት ሲፈጸም በአቅራቢያው የነበሩ ሰዎች የአደጋ ጊዜ ጥሪ ቢያደርጉ ኖሮ ድርጊቱን ማስቆም ይችሉ ነበር" ሲል መግለጫ አውጥቷል።
አንድ የባቡሩ ሠራተኛ የተደፈረችውን ሴት ሲያገኛት ለፖሊስ ደውሎ ወደ ሆስፒታል ተወስዳለች። በወንጀሉ የተጠረጠረውም ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
የ35 ዓመቱ ፊሽተን ንጎይ የተባለው ግለሰብ አስገድዶ የመድፈር እና ሌሎችም ክሶች ይጠብቁታል።
ፖሊስ እንዳለው፤ ባቡር ውስጥ ትንኮሳ ሲደርስባት እና ከዚያም ስትደፈር መንገደኞች ምንም እርዳታ አላደረጉላትም። ከ40 ደቂቃ በላይ የወሰደውን ይህንን አሰቃቂ ድርጊት በአቅራቢያው ሆነው ይመለከቱ የነበሩ ሰዎች ወንጀሉን ሪፖርትም አላደረጉም።
ድርጊቱ ሲፈጸም ምን ያህል መንገደኞች በአቅራቢያዋ እንደነበሩ በትክክል አልታወቀም።
የባቡሩ ፖሊስ ኃላፊ ቶማስ ጄ ነስል "ይህች ሴት ጥቃት ሲደርስባት ሰዎች ስልካቸውን አውጥተው ይቀርጹ ነበር" ብለዋል።
ድርጊቱን በስልካቸው ቀርጸዋል የተባሉ ሰዎች ላይ ምርመራ እየተደገ ይገኛል።
"ሁሉም ሰው ይህንን ድርጊት ተጸይፎ እንዲቆጣ ነው የምንፈልገው። የሰዎች ደኅንነት እንዲጠበቅ ማድረግም አለብን" ብለዋል ኃላፊው።
ኒው ዮርክ ታይምስ ያናገረው ሌላ ፖሊስ ቲሞቲ በርሀርድት እንዳለው፤ ድርጊቱን የቀረጹ መንገደኞች ይከሰሳሉ።
ድርጊቱ ሲፈጸም አይተው አንዳችም እርምጃ ያልወሰዱ ሰዎችን በተመለከተ "እነሱን ለመክሰስ ከባድ ነው" ብሏል።
ምርመራው ሲጠናቀቅ የክሱን ጉዳይ የሚወስነው የዐቃቤ ሕግ ቢሮ እንደሆነ ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም።
ቢቢሲ ያናገረው የዐቃቤ ሕግ ቢሮ "ምርመራ እየተደረገ ነው። ነገር ግን አሁን ባለው ደረጃ መንገደኞች ላይ ክስ ይመሠረታል ተብሎ አይጠበቀም" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
በኬስ ዌስተርን ሪዘርቭ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር እና የቀድሞ ዐቃቤ ሕግ ኬቨን ማክሙንጊል እንደሚሉት፤ በአሜሪካ ሕግ መሠረት መንገደኞች ችግር ውስጥ የገባን ሰው የመርዳታ ሕጋዊ ግዴታ የለባቸውም።
እርዳታ መስጠት የሚጠበቅባቸው ቤተሰቦች፣ መምህራን፣ እንክብካቤ ሰጪዎች እና ፖሊሶች ናቸው።
ፊላደልፊያ ውስጥ የተከሰተው ነገር ለየት ያለ እንደሆነ እና ብዙ ጊዜ መንገደኞች የአደጋ ጊዜ ጥሪ በማድረግ ችግር ውስጥ የገባን ሰው እንደሚረዱ ተናግረዋል።
በማያሚ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህርቷ ታምራ ራይስ እንደሚሉት፤ ድርጊቱ ሲፈጸም በስልካቸው ቪድዮ የቀረጹ ግለሰቦች ለወንጀሉ ተባባሪ ሆነው እስካልተገኙ ድረስ በወንጀል የመጠየቅ እድላቸው ጠባብ ነው።












