ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቦይንግ ቴክኒካል አብራሪ ከ737 ማክስ ደኅንነት ጋር በተያያዘ የፌደራል አቪዬሽንን አጭበርብሯል ተባለ
የቀድሞ የቦይንግ ኩባንያ ቴክኒክ አብራሪ የ737 ማክስ አውሮፕላን ምዘና እና ፍቃድ አሰጣጥ ላይ የአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደርን አጭበርብሯል በሚል ክስ ቀረበበት።
ከሁለት ዓመት በፊት የኢንዶንዢያው ላየን ኤር እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ላይ ከደረሰው አሰቃቂ አደጋ ጋር ተያይዞ አውሮፕላኑ ከበረራ ውጪ እንዲሆን መደረጉ ይታወሳል።
የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ እንዳለው ማርክ ፎርክነር የተባለው የ49 ዓመት የቀድሞ የቦይንግ "ቺፍ ቴክኒካል ፓይለት" ለፌደራል ተቆጣጣሪዎች የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አዲስ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓትን በተመለከተ ሐሰተኛ፣ ትክክል ያልሆነ እና ያልተሟላ መረጃ ሰጥቷል ብሏል።
በዚህም ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ሽጦ ደንበኞቹ ከሆኑ አየር መንገዶች ቢሊዮን ዶላሮችን ሰብስቧል ብሏል።
ፎርክነር ሐሰተኛ፣ ትክክል ያልሆነ እና ያልተሟላ መረጃ በመስጠቱ አብራሪዎች የ737 ማክስ አውሮፕላን የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ላይ ምንም አይነት ስልጠና ሳይወስዱ ቀርተዋል ይላል የፍትሕ ቢሮው መግለጫ።
ንብረትንቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው አውሮፕላን ተከስክሶ ተሳፋሪዎቹ በሙሉ ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ቦይን 737 ማክስ አወሮፕላኖች ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል።
ሚስተር ፎርክነት የአውሮፕላኑን ደኅንነት በተመለከተ በሰጠው አሳሳተ መረጃ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ አስከ 20 ዓመት የሚደርስ ቅጣት ይጠብቀዋል።
የ737 ማክስ አውሮፕላኖች የመከስከስ ምክንያት በአውሮፕላኑ ላይ የተገጠመው ማኒዩቬሪንግ ካራክተሪስቲክስ ኡግሜንቴሽን ሲስተም (ኤምካስ) የተሰኘ አዲስ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ነው ተብሎ ነበር።
"ፎክነር በ737 ማክስ ምዘና እና ፍቃድ ወቅት ሆነ ብሎ ስለ ኤምካስ ቁልፍ የሆኑ መረጃዎችን ከፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር እና ከቦይንግ ደንበኞች ደብቋል" ብለዋል ረዳት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ኬኔዝ ፖላይት።
ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በኢንዶኔዢያ እና ኢትዮጵያ ተከስክሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ አውሮፕላኑ በበርካታ የዓለማችን ክፍል ከበረራ ታግዷል።
የቀድሞ የቦይንግ "ቺፍ ቴክኒካል ፓይለት" በቀረቡበት ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ የሚገኝ ከሆነ በቀረቡበት ክሶች በድምሩ እስከ 100 ዓመት እስር ሊፈረድበት ይችላል ብሏል ዲፓርትመንት ኦፍ ጀስቲስ ባወጣው መግለጫ ላይ።
የአውሮፕላኑን የበረራ ደኅንነት በተመለከተ በአብራሪው ማርክ ፎርክነር የተሰጠው አሳሳች መረጃ ከሁለት ዓመታት በፊት በኢንዶኔዢያና በኢትዮጵያ አየር መንገዶች ላይ ለደረሱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞቱባቸው አደጋዎች ምክንያት ሆኗል ተብሏል።