ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሌባኖስ መዲና ቤይሩት በተከፈተ ተኩስ ሰዎች ተገደሉ
በሌባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት በተከፈተ ጥቃት ቢያንስ ስድስት ሰዎች ሲገደሉ 32 ሰዎች ደግሞ ደግሞ ክፉኛ መቁሰላቸው ተሰምቷል።
ጥቃቱ የተከሰተው የሺያ ሙስሊም ቡድኖች የሆኑት ሄዝቦላህ እና አማል ባለፈው ዓመት የተከሰተውን ፍንዳታ ተከትሎ የተከፈተውን ምርምራ የሚያዩትን ዳኛ እየተቃወሙ ባሉበት ወቅት ነው።
ሄዝቦላህ እና አማል እንደሚሉት የሌባኖስ ኃይሎች የተባለው ፓርቲ አባላት የሆኑ የክርስትና እምነት ተከታይ አልሞ ተኳሾች ናቸው ወደ ሕዝቡ ተኩሰው አመፅ ያስነሱት።
የሌባኖስ ኃይሎች ይህን የሄዝቦላህና አማል ክስ ያጣጥላል።
ባለፈው ዓመት የተከሰተውንና የ219 ሰዎች ሕይወትን የቀጠፈውን ፍንዳታ ተከትሎ እየተደረገ ያለው ምርመራ ቤይሩት ውስጥ ውጥረት ፈጥሯል።
ሄዝቦላህና አጋሮቹ እንደሚሉት ችሎቱን የሚያዩት ዳኛ የሚያዳሉ ቢሆኑም የሟች ቤተሰቦች ግን ዳኛው ንፁሕ ነው ብለው ያስባሉ።
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ነሐሴ ለተከሰተውን የበርካቶችን ሕይወት ላጠፈው አደጋ እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም።
ሐሙስ ዕለት የተከፈተውን ተኩስ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ ዕለተ አርብ የሐዘን ቀን ሆኖ እንዲውል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዝደንት ማይክል አውን በበኩላቸው "ማንም ሰው ሃገሪቱን እንዲያግታትና የራሱ እንዲያደርጋት አንፈቅድም" ብለዋል።
ቤይሩት የሚገኘው ፓላስ ኦፈ ጀስቲስ ከተሰኘው ፍርድ ቤት ፊት ለፊት የተሰባሰቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩት።
ተቃዋሚዎቹ ዳኛ ታሬክ ቢታር ከተሰጠቸው ኃላፊነት እንዲነሱ እየጠየቁ ሳሉ ነው ከባድ የተኩስ እሩምታ መሰማት የጀመረው።
በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ሲሸሹ ሕፃናት ተማሪዎች ደግሞ ከጠረጴዛቸው ሥር ለደበቅ ተገደዋል።
የተኩስ ልውውጡን ለሰዓታት ያደረጉት የሺያ ሙስሊሞች እና ክርስቲያን ታጣቂዎች ናቸው የሚል እምነት አለ።
በዙሪያው ያሉ ትምህርት ቤቶች ያሉ አስተማሪዎች ተማሪዎቻቸው በደረታቸው ወለል ላይ ከጠረጴዛቸው ሥር እንዲነጠፉ አድርገው ነበር ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የሆስፒታልና የጦር ኃይሉ ምንጮች እንዳሉት ከተገደሉት መካከል አብዛኛዎቹ ጭንቅላታቸውን የተመቱ ሲሆኑ መኖሪያ ቤቷ ሳለች በተባራሪ ጥይት የተገደለች ሴትም ትገኝበታለች።
የሌባኖዝ ኃይሎች መሪ ሳሚር ጌጌ የተፈጠረውን ግጭት አውግዘው እርጋታ እንዲሰፍን ጠይቀዋል።
የሃገሪቱ ጦር ኃይል ቦታውን የሚያስሱ ወታደሮች የላከ ሲሆን መንገድ ላይ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ሰው ካዩ እንደሚተኩስ አስታውቋል።
ሐሙስ ዕለት ጠዋት የቀድሞው መንግሥት ሚኒስትሮች የነበሩና የአማል አባላት የሆኑ ሁለት ሰዎች በፍንዳታው ወቅት ቸልተኝነት አሳይተዋል ሲሉ ለጥያቄ እንዲመጡ ዳኛ ቢታር አዘው ነበር።
ምንም ጥፋት የለብንም የሚሉት ሁሉ ባለሥልጣናት ዳኛው እያዳለ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።
የፍንዳታው ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቤተሰቦች ደግሞ ሁለቱ ሰዎች የሚያቀርቡት ቅሬታ ትክክል አይደለም በማለታቸው ምርመራ በሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
ሌባኖስ ለዘመናት አይታ ወደማታውቀው ቀውስ ከገባች ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል።