ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ የጋዝ መስመርን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም እንደሌለባት ጀርመን አስጠነቀቀች
ተሰናባቿ የጀርመን ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ሩሲያ አወዛጋቢውን የጋዝ መስመር ዩክሬንን ለመጉዳት የምትጠቀምበት ከሆነ ተጨማሪ ማዕቀቦች ሊጣሉባት እንደሚችል አስጠነቀቁ።
ሜርክል ከስልጣን ከመውረዳቸው በፊት በኪዬቭ ባደረጉት የመጨረሻ ጉብኝታቸው ኖርድ ስትሪም 2 ተብሎ በሚታወቀው በዚሁ የጋዝ መስመር ላይ ዩክሬን የምታነሳቸውን ጥያቄዎችን እንደሚረዱ ለዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ ነግረዋቸዋል።
የዩክሬኑ መሪ ዘለንስኪ የጋዝ ቱቦው ዝርጋታ በተለይም ሩሲያ በቀጠናው ላይ ያላትን ተጽዕኖ በመጨመር የዩክሬንን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው በማለት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ይህ መስመር በባልቲክ ባሕር ስር የሚያልፍ ሲሆን ሩሲያ ወደ ጀርመን የምትልከውን ጋዝ በእጥፍ ይጨምራል።
የሁለቱ አገር መሪዎች እሁድ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የዩክሬኑ ፕሬዘዳንት ዘለንስኪ "ለመላው አውሮፓ አደገኛ ፕሮጀክት ነው" ሲሉ ገልጸውታል። "የክሬምሊን የጂኦፖሊቲካል መሣሪያ ነው" ሲሉም ፕሬዝደንቱ ተደምጠዋል።
ነገር ግን ከ 16 ዓመታት የሥልጣን ዘመን በኋላ ከስልጣናቸው የሚሰናበቱት ማርኬል አገራቸው የኖርድ ስትሪም 2 በዩክሬን ላይ ጫና ለማሳረፍ ጥቅም ላይ መዋል እንደሌለበት ከአሜሪካ ጋር መስማማታቸውን ተናግረዋል።
ዘለንስኪ በበኩላቸው በዩክሬን ቧንቧዎች በኩል የሚተላለፈው የሩሲያ ጋዝ ውል ከሦስት ዓመታት በኋላ ሲያበቃ ይዞ የሚጣው ጫና እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል።
በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠረው የማስተላለፊያ ክፍያ መቆም የዩክሬን ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ይዞ ይመጣል።
ባሳለፍነው ዓርብ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የተነጋገሩት ሜርክል የዩክሬን ታዳሽ ኃይል ዘርፍን ለማስፋፋት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።
ሩሲያ ከአውሮፓ ሕብረት አገራት የጋዝ ፍጆታ ውስጥ 40 በመቶውን ታቀርባለች። የአዲሱ የቧንቧ መስመር በባልቲክ ስር የሚሄደውን የጋዝ መጠን በዓመት ወደ 55 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ከፍ ያደርገዋል።