ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሊቢያ የባህር ዳርቻ ቢያንስ 57 ስደተኞች ሰምጠው መሞታቸው ተገለፀ
በሊቢያ የባህር ዳርቻ አንዲት ጀልባ መስመጧን ተከትሎ ቢያንስ 57 ስደተኞች መሞታቸውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በትናንትናው ዕለት አስታውቋል።
መርከቧ ከዋና ከተማዋ ትሪፖሊ በስተምስራቅ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሊቢያ ወደብ ክሆምስ ወደብ መስመጧን አይኦኤም አክሎ ገልጻል ፡፡
አይኦኤም በህይወት ከተረፉት ስደተኞች መካከል እንደተረዳው ከሟቾቹ መካከል 20 ሴቶችና ሁለት ህፃናቶች መሆናቸውን ነው።
የአይኦኤም የሊቢያ ተልእኮ ሃላፊ የሆኑት ፌዴሪኮ ሶዳ በትዊተር ገፃቸው ላይ "በሊቢያ የባህር ዳርቻ ሌላ አሳዛኝ የሰው ህይወት መጥፋቱ በጣም አስደንጋጭ ነው" ብለዋል።
ጀልባዋ የሰመጠችበት ምክንያት ባይታወቅም ነገር ግን ከሊቢያ ወደ አውሮፓ የሚጓዙ ጀልባዎች ብዙውን ጊዜ ከአቅም በላይ በመጫን በባህር ዳርቻው ጥበቃ እንዳይገኙ በሚል ምክንያት ጉዟቸውን የሚያደርጉት ምሽት ላይ ነው።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ ዩኤንኤችሲአር መረጃ ከሆነ በዚህ ዓመት ብቻ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ከ 13 ሺህ በላይ ግለሰቦችን ወደ ሊቢያ መመለሱን የገለጸ ሲሆን ፣ በአውሮፖውያኑ 2020 ውስጥ ከተጠለፉትና ፣ ከታደጋቸውው አጠቃላይ ሰዎች ቁጥርም በላይ ነው ተብሏል።
በርካታ ስደተኞች ይህንን አደገኛ ጉዞ በሚያደርጉበት ወቅት የሚሰምጡ ሲሆን ሌሎቹም ወደ ባህር ዳርቻው በሚመለሱበት ወቅት ብዙውን ጊዜ እስር እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ይደርስባቸዋል ፡፡
ዓለምአቀፍ ኤጀንሲዎች አብዛኛውን ጊዜ ከባህር የሚጠለፉ ስደተኞችን ወደ ሊቢያ መመለሳቸውን በተደጋጋሚ አውግዘዋል ፡፡
በዚህ ወር አለም አቀፉ ተሟጋች አምነስቲ በሰጠው መግለጫ 'የሜድትራንያንን ባህር ሲያቋርጡ በተጠለፉ ወንዶችና ሴቶች እና ልጆች ላይ የወሲብ ጥቃትን ጨምሮ አስከፊ ጥሰቶችን የሚያሳይ አዲስ ማስረጃ አለ' ብሏል።
የመብት ተሟጋች ቡድኑ ስደተኞችን በባህር ላይ ለመያዝ እና በግዳጅ ወደ ሊቢያ እንዲመለሱ ለማድረግ የአውሮፓ ኃይሎች ከሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ጋር እንዳይተባበሩ ጠይቋል።
ሊቢያ በሜድትራንያን ባህር በኩል አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመድረስ ለሚሞክሩ ስደተኞች ዋና መተላለፊያ ናት።
ሙአመር ጋዳፊ በናቶ በተደገፉ ኃይሎች በአውሮፓውያኑ 2011 ከተወገዱ ወዲህ ሀገሪቱ በሁከትና ብጥብጥ ስትታመስ ቆይታለች።