በታዋቂ የእንግዳ ማረፊያ ውስጥ ለተደፈረች ቱሪስት 7 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ተከፈለ

ታትሟል

ታዋቂው የእንግዳ ማረፊያ ቤቶች መፈለጊያ የመረጃ መረብ መድረክ ኤርቢንቢ በኒው ዮርክ ከተማ የሚገኝ ማረፊያ የተከራየች የአንዲት ቱሪስት ከተደፈረች በኋላ 7 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንደከፈለ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ይገኛሉ።

ብሉምበርግ እንደዘገበው ከአምሰት ዓመታት በፊት በ2015 (እአአ) የአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ጥቃት የደረሰባት አንዲት አውስትራሊያዊት ተጓዥ ክፍያውን እንደተቀበለች ተነግሯል።

ጥቃጡ ተፈፀመባት ሴት እና ጓደኞቿ ጥቃቱ በተፈፀመ ምሽት በቤቱ አቅራቢያ ከሚገኝ ሱቅ ነበር ቁልፍ ወስደው ወደተከራዩት ክፍል የሄዱት። ተጠርጣሪው ጥቃቱን ከመፈጸሙ በፊት የአፓርታማውን ቁልፎች ቅጂ አሰርቶ መያዙን ሪፖርቱ ይጠቁማል ።

ቱሪስቷ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ወደ ክፍሏ የተመለሰች ሲሆን የ24 ዓመቱ ጥቃት ፈፃሚ ጁኒየር ሊ በመጸዳጃ ቤት ውስጥ ተደብቆ እንደጠበቀ ብሉምበርግ ዘግቧል።

በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኘው ግለሰብ የአስገድዶ መድፈር ክስ የቀረበበት ሲሆን ጥፋቱን አልፈፀምኩም ሲል ክዷል።

ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላ የኤርቢንቢ የደኅንነት ቡድን የአካባቢውን የፖሊስ ኃላፊዎች ያነጋገረ ሲሆን ድጋፍ ለመስጠት ጥያቄ አቅርቦ ተጎጂዋን ወደ ሆቴል በመውሰድ አሳርፏል።

እንዲሁም እንደ የሥነ ልቦና ድጋፍ ያሉ ወጪዎችን ለመሸፈን ጥሪ ያቀረበ ሲሆን የተጠቂዋን እናት ከአውስትራሊያ ወደ አሜሪካ ለማምጣት ወጪዎችን ሸፍኗል ።

ብሉምበርግ እንደገለፀው ኤርቢንቢ ሰባት ሚሊዮን እንዲከፍል ያደረገው ይህ የስምምነት ውል ተጎጂዋ ኤርቢንኒንም ሆነ የአፓርታማውን ባለቤት እንዳትከስ የሚያደርግ ነው።

እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስም ሁለት ዓመት ፈጅቷል።

ብሉምበርግ በዚህ የኪራይ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ላይ ባደረገው ጠለቅ ያለ የምርመራ ዘገባ ላይ ነበር ይህ ዜና የተካተተው።

ድርጅቱ ከዚህ አጋጣሚ በኋላም ቢሆን ደንበኞች የክፍላቸውን ቁልፍ የት እንደሚያስቀምጡ በተመለከተ ያለውን የደኅንነት አጠባበቅ ደንቡን እንዳላሻሻለ ተገልጿል።

ማረፊያ ቤቶቹን የሚያከራዩ ሰዎች የስማርት ቁልፈችን እንዲጠቀሙ የማይገደዱ ሲሆን የሚጠቀሙትም ደንበኞቻቸው ሲቀየሩ የይለፍ ቁጥር ለመቀየር አይገደዱም።

ሆኖም እንደ ስማርት መቆለፊያዎች እና እንደ ድምፅ መመርመሪያ ያሉ እቃዎችን ለመግዛት ለሚፈልጉ ሆቴሎች ከፍተኛ ቅናሽ እንደሚደረግላቸው ዘገባው ያትታል ።