ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናይጄሪያ ትዊተርን 'ላልተወሰነ ጊዜ' ልታግድ ነው
የናይጄሪያ መንግሥት የትዊተርን "ላልተወሰነ ጊዜ" ሊያገደ ነው ሲል የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር አስታወቁ።
አርብ ዕለት ይፋ በተደረገ መግለጫ እገዳው ተፈጻሚ የሚሆነው "ማህበራዊ ሚዲያው ቀጣይነት ባለው መንገድ ... የናይጄሪያን ህልውና ሊያናጋ ይችላል" በሚል ምክንያት ነው።
ናይጄሪያ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ጋና የአፍሪካ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱን ለመክፈት እቅድ ያለው ትዊተር የናይጄሪያን መንግሥት መግለጫ "እጅጉን አሳሳቢ ነው" ብሏል።
የናይጄሪያ መንግሥት ውሳኔ የተሰማው ፕሬዝደንት ሙሃሙዱ ቡሃሪ በትዊተር ገጻቸው ላይ አጋርተው የነበረው መልዕክት የትዊተር ሕግጋትን የተላለፈ ነው በሚል ከገጹ እንዲጠፋ ከተደረገ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
የትዊተር ቃል አቀባይ የፕሬዝደንቱ ጽሑፍ "የትዊተርን ህጎች የጣሰ ነው። የገጹ ባለቤት ህግ የጣሰውን ትዊት እንዲያጠፋ እና ማንበብ እንጂ መጻፍ እንዳይችል ተደርጎ ለ 12 ሰዓታት እንዲቆይ ይደረጋል" ብለው ነበር። ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ግን አልተሰጠም።
የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ ላኢ መሐመድ ከዚህ ቀደም የአሜሪካውን ግዙፍ ማህበራዊ ሚዲያ ውሳኔን "ባለሁለት መልክ" ብለውታል።
አርብ በተሰጠው መግለጫ የናይጄሪያ እገዳ በተግባር እንዴት እንደሚሠራ ወይም ትዊተር የናይጄሪያን ህልውና እንዴት እንዳናጋው የሚገልጽ ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።
መግለጫው አክሎም የናይጄሪያ ብሔራዊ የብሮድካስቲንግ ተቆጣጣሪ ኤን .ሲ "በናይጄሪያ ለሁሉም የበይነመረብ መረጃ አስተላለፊዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ ሥራዎች ፈቃድ መስጠት" እንዲጀመር ተነግሮታል ብሏል።