ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአውሮፓ ሕብረት የቤላሩስ አውሮፕላኖች በአየር ክልሉ እንዳይበሩ አገደ
ከሳምንታት በፊት የቤላሩስ ባለስልጣናት ጋዜጠኛውን ለማሰር የራይንኤር የመንገደኞችን አውሮፕላንን አስገድደው ማሳረፋቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ሕብረት የቤላሩስ አውሮፕላኖች በአየር ክልሉ እንዳይበሩ አገደ።
የሕብረቱ አባላ አገራት አውሮፕላኖችም የቤላሩስ የአየር ክልልን እንዳይጠቀሙ አበረታታለሁ ብሏል የአውሮፓ ሕብረት።
የአውሮፓ ሕብረት የአቪዬሽን ደህንነት ኤጀንሲ የሕብረቱ አባል አገራት አየር መንገዶች ለአደጋ ጊዜ ካልሆነ በቀር የቤላሩስን የአየር ክልል እንዳይጠቀሙ መመሪያ አውጥቷል።
ይህ መመሪያ በየቀኑ ከ400 በላይ የቤላሩስን የአየር ክልል የሚያቋርጡ የመንገደኞች አውሮፕላኖች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል ተብሏል።
የጀርመኑ ሉፍታንዛ እና የፈረንሳይ አየር መንገዶች በቤላሩስ አየር ክልል ላይ እንደማይበሩ ከወዲሁ አስታውቀዋል።
የቤላሩስ ባስልጣናት ተቃዋሚውን ጋዜጠኛ ለማሰር ሲሉ የመንገደኞች አውሮፕላን በቤላሩስ መዲና አስገድደው ማሳረፋቸው የአውሮፓ አገራትን እጅጉን ያስቆጣ ተግባር ሆኖ አልፏል።
የ26 ዓመቱ ሮማና ፕሮታሴቪች ከግሪክ ወደ ሉቲኒያ እየበረረ ሳለ ነበር አውሮፕላኑ በቤላሩስ መዲና ሚንስክ እንዲያርፍ የተደረገው።
አውሮፕላኑ ካረፈም በኋላ ጋዜጠኛው እና ፍቅረኛው በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ትናንት ደግሞ በቤላሩስ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛው ጸረ-መንግሥት ተቃውሞዎችን ስለማስተባበሩ እያለቃሰ ቃሉን ሰጥቷል። የጋዜጠኛው ቤተሰብ ግን ሮማኖ ይህን ቃል እንዲሰጥ በባለስልጣናት ማስፈራሪያ እና ጫና ደርሶበታል ይላሉ።
የአውሮፓ ሕብረት በቤላሩስ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን የመጣል እቅድ ያለው ሲሆን ከእነዚህም መካከል የቤላሩስ አውሮፕላኖች የአውሮፓ ሕብረት አየር ክልልን እንዳይጠቀሙ መከልከል አንዱ ነው።
ይህ ክልከላ ከትናንት ምሽት ጀምሮ ተፈጻሚ መሆን የጀመረ ሲሆን፤ በእግዱ መሠረት የቤላሩስ አውሮፕላኖች በአውሮፓ ሕብረት አገራት ውስጥ ማረፍ፣ መነሳት እና የአየር ክልል መጠቀምን ይከለክላል።
ቤላቪያ የተሰኘው የቤላሩስ አየር መንገድ ሚላን፣ በርሊን፣ ፓሪስ፣ ሮም እና ቬይናን ጨምሮ በአውሮፓ ወደ 20 የሚጠጉ መዳረሻዎች ነበሩት።