እግር ኳስ፡ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ባለቤቶቹ ላይ ለምን አመጹ?

Sport

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ትናንት ከሰአት ላይ የኦልድትራፎርድ መግቢያ በሮች አካባቢ ከባድ ጩኀትና ጭስ ይስተዋል ነበር።

አብዛኛዎቹ ደጋፊዎች ስታዲየሙ ዙሪያ ተቃውሟቸውን እየገለጹ የቆዩ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ጥሰው በመግባት መጫወቻ ሜዳው ላይ ተሰባስበው ታይተዋል።

አብዛኛዎቹ ደጋፊዎች በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንዶች ነበሩ ተብሏል። ነገር ግን ሴቶችና በእድሜ የገፉ ደጋፊዎችም ከተቃዋሚዎቹ መካከል ነበሩ።

አንድ በ50ዎቹ አልያም በ60ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ግለሰብ አረንጓዴና ወርቅማ ቀለም ያለው ስካርፍ አንገቱ ላይ አድርጎ ይታያል። ይሄው ግለሰብ የስታዲየሙን ግቢ ለቅቆ ከወጣ በኋላ የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋቾችን የያዘችው ባስ እስክትመጣ ከሚጠባበቁት ደጋፊዎች ጋር ተቀላቀለ።

ቁጣ አይታይበትም፤ ከደጋፊዎችና ከመገናኛ ብዙሀን ጋር ሲያወራም በተረጋጋ መንፈስ ነው። አብዛኛዎቹ ሜዳ ውስጥ ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ በጉጉት ሲጠባበቁ የነበረ ሲሆን እሱም ስላለው ሁኔታ ያስረዳቸው ነበር።

ዕሁድ ዕለት ማንቸስተር ዩናይትድ ከታሪካዊ ተቀናቃኘኙ ሊቨርፑል ሊያደርገው በነበረው ጨዋታ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በመሰባሰብ ተቃውሟቸውን እንደሚገልጹ ሲጠበቅ ነበር። ነገር ግን ተቃውሞው ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ጨዋታው ለሌላ ጊዜ እስከመተላለፍ ይደርሳል ብሎ ግን ማንም አልጠበቀም ነበር።

ልክ እንደ ሌሎቹ አምስት ትልልቅ ክለቦች ደጋፊዎች የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎችም ከሱፐር ሊግ ሀሳብ ጋር በተያያዘ ቁጣቸውን ሲገልጹ ነበር። የሱፐር ሊግ ውድድር ላይ መሳተፍ እንደማይፈልጉ ገልጸውም ነበር።

ነገር ግን የማንቸስተር ዩናይትድን ደጋፊዎች ለየት የሚያደርጋቸው መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉት የክለቡ ባለቤት የሆኑት የግሌዘር ቤተሰቤች ውሳኔ አላስገረማቸውም ነበር። ከጅምሩ የግሌዘር ቤተሰቦች ክለባችንን ይልቀቁልን የሚል ጥያቄ ማሰማት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

አብዛኛዎቹ ደጋፊዎች የክለቡ ባለቤቶች የ149 ዓመታት እድሜ ያስቆጠረው ክለብ ታሪክ ከምንም እንደማይቆጥሩትና ዋነኛ ዓላማቸው ገንዘብ ማግበስበስ ነው ይላሉ። ደጋፊዎቹ ሲከራከሩም ባለቤቶቹ ስለክለቡ የሚጨቁ ቢሆን ኖሮ ክለቡን በአውሮፓውያኑ 2005 ከገዙት በኋላ 790 ሚሊየን ፓውንድ እዳ ባልተመዘገበ ነበር ይላሉ።

ማንቸስተር ዩናይትድ በግሌዘር ቤተሰቦች ከመገዛቱ በፊት ለገበያ ሲቀርብ ምንም አይነት እዳ ያልነበረበት ተቋም እንደነበር ባሳለፍነው ወር የወጣ ሪፖርት ያሳያል። ደጋፊዎች ደግሞ ክለቡ የሚያገኘውን ገንዘብ በሙሉ የግሌዘር ቤተሰቦች እየወሰዱት እንደሆነና ክለቡ ምንም እየተጠቀመ እንዳልሆነ ይገልጻሉ።

በአሁኑ ሰአት የክለቡ ይፋዊ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ማንቸስተር ዩናይትድ ያልተከፈል 455 ፓውንድ እዳ ያለበት ሲሆን የግሌዘር ቤተሰቦች ከገዙት በኋላ ደግሞ ከ1 ቢሊየን ፓውንድ በላይ ወጪ አድርጓል።

በእነዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት ደጋፊዎች ቁጣቸውን መግለጽ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። በቀድሞው ታሪካዊ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ዘመን እንኳን ተቃውሞዎች ይነሱ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ፈርጉሰን ባለቤቶቹን አይተቹም ነበር። እንደውም በዝውውር መስኮት ወቅት የግሌዘር ቤተሰቦች ከፍተኛ እርዳታ እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ ይገልጹ ነበር።

አንዳንድ ደጋፊዎች ደግሞ የፈርኡሰን ብስለትና ልምድ የባለቤቶቹን ችግር እንዳናስተውል አድርጎን ነው እንጂ ባለቤቶቹ ከራሳቸው ትርፍ ውጪ ስለክለቡ ከድሮ ጀምሮ አይጨነቁም ይላሉ።

ነገር ግን እዚህ ጋር ሌላ መከራከሪያ የሚያቀርቡም አልጠፉም። የግሌዘር ቤተሰቦች ማንቸስተር ዩናይትድን ከገዙ በኋላ ክለቡ ከፍተኛ የሚባል ትርፍ ማግኘት ችሏል። ከሌሎቹ ትልልቅ ክለቦች በተለየ መልኩም እንደ አዲዳስና ቼቭሮሌት ከዋና ዋና ስፖንሰሮች በተጨማሪ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎችም ስር የሰደደ የንግድ ቁርኝት ፈጥረዋል።

በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ እሲያና አፍሪካ ከሚገኙ የተለያዩ ድርጅቶች ጋር የንግድ ስምምነት ተፈራርመዋል። ክለቡ ያለውን ተወዳጅነት በመጠቀም ከፍተኛ ትርፍ እንዲገኝም አድርገዋል። ይህ በመጥፎ መወሰድ የለበትም የሚሉም አልጠፉም።

ለዚህም ነው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማንቸስተር ዩናይትድ የእግር ኳስ ክለብ ውስጥ የታየው ትርፈፋማነትና ስኬት ከግሌዘር ቤተሰቦች ጋር የተያያዘ ነው የሚባለው።

ከዚህ በተጨማሪ ደጋፊዎች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል አንደኛው ከተጫዋቾች ግዢ ጋር የተያያዘ ነው። በርካታ ደጋፊዎች የግሌዘር ቤተሰቦች ክለቡን የሚመጥኑ ተጨዓዋቾች እንዲገዙ የሚፈቅድ ስርአት አልገነቡም ይላሉ። ''ከክለቡ አጨዋወት ጋር የሚሄዱ ተጫዋቾች ከተለዩ በኋላ ብዙ ጊዜ ተጫዋቾቹ ወደ ክለቡ አይመጡም፤ አልያም የመጀመሪያ ምርጫ ያልሆነ ተጫዋች ይገዛል'' ሲል አንድ ደጋፊ በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ምሬቱን ገልጿል።

የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ኦሌ ጎነር ሶልሻየርም ቢሆን ከትችት አላመለጠም። እሱም ልክ እንደ ቀድሞው አሰልጣኝ አሌክስ ፈርጉሰን የግሌዘር ቤተሰቦችን በይፋ አይተችም። በዚህም መክንያት ደጋፊዎች አሰልጣኙን በተደጋጋሚ ይተቹታል።

ይህ በንዲህ እንዳለ ሶልሻየር ከሊቨርፑል ጋር ሊደረግ የነበረው የእሁዱ ጨዋታ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ተከትሎ ''የደጋፊዎች ድምጽ መሰማት አለበት'' ብሏል