ኮሮናቫይረስ፡ ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ እና ጭምብል ማድረግ ለዓመታት ሊዘልቅ እንደሚችል ተጠቆመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእግሊዝ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ማድረግ ብሎም ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ለዓመታት ሊቀጥል እንደሚችል የአገሪቱን የክትባት ዘርፍ የሚመሩ ባለሙያ ገለፁ።
በእንግሊዝ የጤና ሚኒስቴር ውስጥ የክትባት ዘርፍ ሃላፊ የሆኑት ዶክተር ሜሪ ራምሴ ሌሎች አገራት የክትባት ዘመቻቸውን በስኬት እስከሚያጠናቅቁ እና ይህንንም ተከትሎ ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ እነዚህ ገደቦች ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ብዙ ሰው የሚታደማቸው ዝግጅቶች ጥንቃቄ የተሞላበት የደህነንት መመሪያዎች ትግበራ እና ክትትል እንደሚያስፈልጋቸውም ተናግረዋል።
ዶክተር ራምሴ እንዳሉት በተለይም ጭምብሎችን እንደማድረግ ያሉ ገደቦች በማህበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነትን እያገኙ የመጡ ሲሆን ይህም በተለይ ኢኮኖሚው እንዲንቀሳቀስ እድል ከፍቷል ብለዋል።
‹‹ሰዎች ከእንዲህ ያሉ ገደቦች ጋር እየተለማመዱ አብረዋቸው መኖር ይችላሉ። ኢኮኖሚውም ከባድ ካልሆኑ ክልከላዎችን ጋር መንቀሳቀስ ይችላል›› ብለዋል።
‹‹የኮሮናቫይረስ ቁጥር በሌላው ዓለም እስከሚቀንስ እና ክትባት በበቂ ሁኔታ እስከሚዳረስ ድረስ እነዚህ ገደቦች በእርግጠኝነት ለተወሰኑ ዓመታት የሚቀጥሉ ሲሆን ቀስ በቀስ ወደ መደበኛ ህይወት እንመለሳለን›› ሲሉም ጨምረው ገልፀዋል።
ዶክተር ራምሴ ጨምረው ቫይረስ በቀላሉ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ሊያጠቃ ስለሚችል ‹‹በችኮላ ወደ መዘናጋት መግባት የለብንም›› ሲሉም አሳስበዋል።
የእንግሊዝ መንግሥት ዋና የጤና አማካሪ ፕሮፌሰር ክሪስ ዊቲ በያዝነው ወር መጀመሪየ ላይ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ እጅ መታጠብ፣ ጭምብል ማጥለቅ፣ ምርመራ በማድረግ መለየት እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ክትባት መጀመር ቫይረሱን ከበጋው ወራት በፊት ለመቆጣጠር ያግዛል የሚል ተስፋ ተጥሎ ነበር ብለዋል።
መንግሥትን የሚያማክሩ የሳይንትስቶች ቡድንም የቫይረሱን ስርጭት ሊቀንሱ የሚችሉ መሰረታዊ የሆኑ ፖሊሲዎችን መተግበር ለተወሰነ ግዜ አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው ነበር።
እነዚሁ ባለሙያዎች በምርመራ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መለየት፣ ራስን በለይቶ ማቆያ ውስጥ ማቆየት፣ በፈቃደኘነት የሚደረጉ እና በሽታውን አደጋዎች ለመቀነስ የሚያበረታቱ ሕዝባዊ መልዕክቶች ሊቀጥሉ እንደሚችሉም ተናግረው ነበር።
የእንግሊዝ መንግሥት የእንቅስቃሴ ገደቦችን ቀስ በቀስ ለማንሳት ያዘጋጀው ፍኖተ ካርታ እንደሚለው ማህበራዊ መራራቅን የሚያስገድዱ ሕጋዊ ግዴታዎች ከሰኔ 14 በፊት እንደማይነሱ ያስረዳሉ።












