ቮልቮ በ2030 ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ መኪኖች ምርት ሊገባ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግዙፉ የመኪና አምራች ኩባንያ ቮልቮ በ2030 የሚያመርታቸውን ተሽከርካሪዎች በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ለማድረግ ወሰነ።
የሰዊድኑ ኩባንያ በዘጠኝ አመት ግዜ ውስጥ በአሌክትሪክ ኃይል ከሚሰሩ ውጪ ያሉ መኪኖቹን በሙሉ ከገበያ እንደሚያስወጣ አስታውቋል።
ኩባንያው ከዚህ ውሳኔ የደረሰው የአሌክትሪክ መኪኖች ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ መሆኑን አስታውቋል። ቻይና የኩባንያው ዋና የገበያ መዳረሻ እንደምትሆንም ተጠቁሟል።
ኤሌክትሪክ መኪኖች በኤሌክትሪክ ሃይል በተሞላ ባትሪ ይሽከረከራሉ። በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰሩ መኪኖች በአከባቢ አየር ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ አነስተኛ በመሆኑ መንግሥታት የመኪና አምራቾች በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖችን በኤሌክትሪክ ኃይል በሚንቀሳቀሱ መኪኖች እንዲተኩ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።
ለአብነትም ዩናይትድ ኪንገደም በ2030 በቤንዚን ወይም ናፍጣ ብቻ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን እንደምታግድ ከዚህ ቀደም ይፋ አድርጋለች።
ቮልቮ ኩባንያ በእአአ 2025 ለገበያ ከሚያቀርባቸው ተሽከርካሪዎች ግማሽ ያክሉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ እንደሚሆኑ አቅዶ ነበር።
ከቮልቮ በተጨማሪ በርካታ ግዙፍ መኪና አምራች ኩባያዎች ምርቶቻቸውን ወደ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ለማድረግ ወጥነዋል።
የፈረንሳይ እና ጃፓን ኩባንያ የሆኑት ሬኖልት እና ኒሳን እአአ 1999 ላይ ጥምረት ለመመስረት ከተስማሙ በኋላ በርካታ የአሌክትሪክ መኪኖችን ለገበያ በማቅረብ ቀዳሚ ናቸው።
በአለም ላይ ቁጥር አንድ በሆነው ቢሊየነሩ ኤለን መስክ የሚተዳደረው ቴስላ ኩባንያ ደግሞ ቁጥር ሁለተኛው ግዙፍ የአሌክትሪክ መኪኖች አቅራቢ ድርጅት ነው።
ቴስላ የሚያመርታቸው የአሌክትሪክ መኪኖች በአንድ ሙሊት በሰዓት 140 ኪ.ሜ ፍጥነት እየተሽከረከሩ ከ500 ኪ.ሜትር በላይ መጓዝ ይችላሉ።












