የነዳጅ ዋጋ ከወረርሽኙ በፊት ወደነበረበት አሻቀበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የነዳጅ ዋጋ ባለፈው ዓመት የተከሰተውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ በታሪክ ዝቅተኛ የተባለውን ዋጋ አስመዝግቦ ነበር።
በእርግጥ ከበፊቱ አንጻር ሲወዳደር የነዳጅ ፍላጎት አሁንም ዝቅ ያለ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ክትባቶች መሰራጨታቸውን ተከትሎ ተስፋ ሰጪ መነቃቃት ታይቶበታል።
በአብዛኛው የነዳጅ ዋጋ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ መለኪያ ተደርጎ ይወሰዳል። ቫይረሱ እንዲቀንስ የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ አሁን የሚታየው መነቃቃት ለነዳጅ አምራቾች ተስፋ ሰጭ ሆኗል።
"ጥቁር ወርቅ" በመባል የሚታወቀው ነዳጅ፣ ባለፉት ጥቂት ወራት ከ50 በመቶ በላይ ጭማሪ አድርጎ የአንድ በርሚል ነዳጅ ዋጋ 60 ዶላር ደርሷል።
በኃይል አቅርቦት ገበያ ላይ ሁነኛ የለውጥ ማጠንጠኛ ተደርጎ የሚወሰደው ድፍድፍ ነዳጅ በአሁኑ ወቅት ጠንካራ የሚባል እድገት እያሳየ ነው። ወደፊት ለሚደረጉ ትዕዛዞች ከባለፈው ሕዳር ወር ጀምሮ እስከ 59 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በአሜሪካ የነዳጅ ገበያ እንደመለኪያ በሚታየው ዌስት ቴክሳስ ኢንተርሚዴት የአንድ በርሚል ነዳጅ ዋጋ ከአንድ ዓመት በኋላ ባለፈው ሳምንት 55 ዶላር ደርሶ ነበር።
ቫንዳና ሃሪ የተባሉ ሲንጋፖር የሚገኝ የነዳጅ ኩባንያ ባለቤት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ኮሮናቫይረስ በክትባት ምክንያት ሊገታ ይችላል የሚለው አስተሳሰብ በነዳጅ እና ሌሎች የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ላይ መነቃቃት በማሳየቱ የነዳጅ ዋጋ ባለፉት ሳምንታት የማሻቀቡ ሁነኛ ምክንያት ነው።
ፍላጎቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን በተለይ በእሲያ ፍላጎቱ ከፍ ያለ መሆኑንና በቻይና የሚታየው ሁኔታም ተስፋ ሰጪ መሆኑን የዘርፉ ተሳታፊዎች ማረጋገጫ እየሰጡ ነው።
በእርግጥ የነዳጅ አምራች አገሮች እና የነዳጅ ላኪ ድርጅቶችም ለነዳጅ ዋጋው ማንሰራራት ቀላል የማይባል አስተዋጽዖ አላቸው።
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር በወረርሽኙ ሳቢያ የተፈጠረውን የዋጋ ቅናሽ ለማስተካከል ሲባል ነዳጅ አምራቾች ባደረጉት ምርትን የመቀነስ ስምምነት መሰረት በአጠቃላይ 2 ነጥብ አንድ ቢሊዮን የነዳጅ ምርት ወደ አክስዮን ገበያ እንዳይገባ ተደርጓል።
ከቢሊዮን በርሚል በላይ ወደ ገበያ እንዳይቀርብ በማድረግ የወረርሽኙ መከሰት ያስከተለው ተጽጽዕኖ ታሪካዊ የሚባል ነው።
በተለይ በአውሮፕላን ኢንዱስትሪው በኩል በረራዎች መቆማቸውን ተከትሎ ባለፈው ዓመት እጅግ ከፍተኛ የተባለው የነዳጅ ፍላጎት ቅናሽ ታይቶበታል። እንደ ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማሕበር መረጃ ከሆነ የአየር በረራ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ70 በመቶ ቀንሷል።
በሌሎች ዘርፎች ላይ ግን ፍላጎት ጭማሪ አሳይቷል።
ፈላጊዎች ምርቶቻቸውን የሚያዙት በበይነ መረብ ነው። ይህ ደግሞ ምርቶቻቸውን ለማጓጓዝ እንደ ተሽከርካሪ፣ መርከብ እና ባቡር የመሳሰሉትን በመጠቀማቸው ነዳጅ በእነዚህ ማጓጓዣዎች ዘንድ ተፈላጊነቱ እንዳይቀንስ አድርጓል።
የኢ-ኮሜርስ ግብይትም ሌላኛው ለነዳጅ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ መቆየት አንዱ ምክንያት ነው።
ባለፈው ወር ዓለም አቀፉ የኢነርጅ ኤጀንሲ እንዳስጠነቀቀው የነዳጅ ዋጋ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት ወደነበረበት ዋጋ ለመመልስ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ብሎ ነበር።












