ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቃለ መሐላ መፈጸም ያቃታቸው የሕዝብ እንደራሴ ተባረሩ
ቃለ መሐላ በአግባቡ መፈጸም የተሳናቸው አንድ የታንዛንያ የሕዝብ እንደራሴ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል።
የሕዝብ እንደራሴው የተሰጣቸውን ኃላፊነት ከመረከባቸው በፊት በይፋ ቃለ መሐላ ለማድረግ በስብሰባ አዳራሽ ተገኝተው ነበር።
ተመራጩ የሕዝብ እንደራሴ ስማቸው ሲጠራ ከታዳሚው መካከል ወጥተው ወደ መድረኩ አቅንተዋል።
በማዕድን ሚንስትር በተባባሪ ሚንስትርነት ተመርጠው የነበሩት ፍራንሲስ ዱላኔ፤ ቃለ መሐላውን መፈጸም ተስኗቸዋል።
በቃለ መሐላው የተካተቱ አረፍተ ነገሮችን ለማንበብ ሲያንገራግሩ፣ ቃላት ለማውጣት ተቸግረው ሲንተባተቡም ነበር።
የታንዛንያው ፕሬዘዳንት ጆን ማጉፉሊ በተገኙበት መርሃ ግብር፤ የሕዝብ እንደራሴው ቃለ መሐላውን ለመፈጸም ተቸግረው ሲንተባተቡ የሚያሳይ የሦስት ደቂቃ ቪድዮ በትዊተር ተለቋል።
ቪድዮው ላይ አዲስ ተመራጩ የሕዝብ እንደራሴ በተደጋጋሚ ቃላት ለማውጣት ሞክረው አልሳካ ሲላቸው ይታያል።
ከደቂቃዎች በኋላ የሕዝብ እንደራሴው ፍራንሲስ ዱላኔ ወደመቀመጫቸው እንዲመለሱና ለሌሎች የሕዝብ እንደራሴዎች መድረኩን እንዲለቁ ተደርጓል።
ፕሬዘዳንት ጆን ማጉፉሊ፤ ለሥራው ማመልከቻ ያስገቡ ሰዎችን የሥራ ልምድ ከገመገሙ በኋላ እንደመረጧቸው ተናግረዋል።
ሆኖም ግን በማዕድን ሚንስትር በተባባሪ ሚንስትርነት ተመርጠው የነበረው ፍራንሲስ በሌላ የሕዝብ እንደራሴ እንደሚተኩ ፕሬዘዳንቱ አስታውቀዋል።
"ይህንን ሥልጣን ቃለ መሐላ በአግባቡ መፈጸም ለሚችል ሰው እሰጣለሁ" ብለዋል ፕሬዘዳንቱ።
ፍራንሲስ የሕዝብ እንደራሴ መቀመጫውን ይዘው መቆየት ቢችሉም በሌላ ሰው እንደሚተኩ ተነግሯቸዋል።
ከሥራቸው የተባረሩት የሕዝብ እንደራሴ ለምን ቃለ መሐላውን በአግባቡ ለመፈጸም እንደተቸገሩ አላብራሩም።