የጋና ፕሬዝደንት አኩፎ-አዶ ዳግም ተመረጡ

ታትሟል

የጋናው ፕሬዝደንት ናና አኩፎ-አዶ ሰኞ ዕለት የተካሄደውን ምርጫ በጠባብ ውጤት በማሸነፍ በድጋሚ ፕሬዝደንት በመሆን ተመረጡ።

አኩፎ-አዶ ከተሰጠው አጠቃላይ ድምጽ 51.6 በመቶ ድምጽ ሲያገኙ ተቀናቃኛቸው የቀድሞ ፕሬዝደንት ጆን ማሃማ 47.4% በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን ይፋዊ ውጤቶች አመልክተዋል።

የፕሬዝደንቱ ተቀናቃኝ እስካሁን ሽንፈታቸውን አልተቀበሉም።

በአፍሪካ የተረጋጋ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት አላት ተብላ በምትወደሰው ጋና ሁለቱ ፖለቲከኞች በፕሬዝደንታዊ ምርጫ ሲፎካከሩ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።

የምርጫው የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ውጤት እስካሁን ይፋ ባይሆንም ተቀራራቢ ውጤት ሊመዘገብ እንደሚችል ተገምቷል።

ፕሬዝደንት አኩፎ-አዶ ምርጫውን ለሁለተኛ ጊዜ ማሸነፋቸው ይፋ ሲደረግ በመላው ጋና የፕሬዝደንቱ ደጋፊዎች ደስታቸውን ሊገልጹ አደባባይ ወጥተው ነበር።

በኮሮናቫይረስ የተጎዳውን የጋናን ምጣኔ ሃብት ማነቃቃት እና የስራ አጥ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ የተመራጩ ፕሬዝደንት የቤት ሥራ ይሆናል።

ቀደም ሲል ፖሊስ ከምርጫ ጋር የተያያዙ 21 ግጭቶች ተከስተው አምስት ሰዎች መገደላቸውን አስታውቆ ነበር።

ተቀናቃኙ ጆን ማሃማ ከእአአ 2013 - 2017 ጋናን በፕሬዝደንትነት መርተዋል። ከዚያም መንበረ ስልጣኑን ለአኩፎ-አዶ አሳልፈው ሰጥተዋል።

በዘንድሮ ምርጫ ሁለቱ ተቀናቃኞች በኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት የምርጫ ቅስቀሳቸውን በሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲያደርጉ ቆይተዋል።