ካናዳ፡ አስቤስቶ ከተማ ደንቃራ ሆኖብኛል ያለችውን ስሟን በሕዝበ ውሳኔ ቀየረች

የአስቤስቶስ ከተማ ጽሁፍ

የፎቶው ባለመብት, COURTESY VILLE D'ASBESTOS

ታትሟል

የካናዳዋ ትንሽ ከተማ አስቤስቶስ ስሟን ቀይራለች። ከተማዋ ይህንን ስም ያገኘችው በአስፔስቶ ማዕድን ሃብቷ የተነሳ ነበር።

ይህች ከተማ አሁን ቫል ዴስ ሶርስስ ተብላ ተጠርታለች።

7000 ሰዎች የሚኖሩባት የኪውቤኳ ከተማ በአስቤስቶ ማዕድን ሃብቷ እጅጉን የታወቀች ናት።

ይህች ከተማ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከ አሚንቴ ከተሰኘው የፈረንሳይ ስሟ ገኖ አስቤስቶስ የሚለው ስሟ ተሰጥቷታታል።

የከተማው ምክር ቤት ግን የውጪ ባለሃብቶችን ለመሳብ ይህ ስሟ 'ደንቃራ ሆኖባታል' በማለት ባለፈው ሕዳር ወር አዲስ ስም እንዲወጣላት ጥሪ አቅርቦ ነበር።

ከተማዋም ሰኞ ዕለት ምሽት እድሜያቸው 14 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሁሉ አዲሱን ስሟን እንዲመርጡ አድርጋ ውጤቱ ይፋ ተደርጓል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ረዥም ጊዜ የፈጀ ንግግር ከዚያም ደግሞ ምርጫ አድርገዋል።

ምርጫው 14 ዓመት የሞላቸው አፍላ ጎረምሳ ዜጎቿንም ይጨምር ነበር።

በከተማዋ እድሜያቸው ለመምረጥ ከደረሰ ዜጎች መካከል ግማሽ ያህሉ መርጠዋል ተብሏል።

ከዚያም ቫል ዴስ ሶርስስ የሚለው አብላጫውን ድምጽ በማግኘት ተመርጧል።

ይህ ስም በሶስተኛው ዙር ምርጫ 51 በመቶ አግኝቶ ነው የተመረጠው።

የከተማዋ ከንቲባ የሆኑት ሁገስ ግሪማርድ እንዳሉት አዲሱ ስም "ለወደፊቱ ተስፋ ሰጪ ነው።"

ለከተማዋ ስም ይሆናሉ ተብሎ ከተዘረዘሩት መካከል ላአዙር ዴስ ካርንቶንስ፣ ጄፍሪ ሱር ሌ ላክ፣ ላሮሼሌ፣ ፊኒክስ እና ትሮይስ ላክስ ይገኙበታል።

አስቤስቶስ ስሟን በይፋ ለመቀየር እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ትጠብቃለች ተብሏል።

" ጥሩ የገና ስጦታ ሊሆን ይችላል" ብለዋል ከንቲባዋ።

የአስቤስቶስ ማዕድን ማውጣት እኤአ በ2011 እስኪቋረጥ ድረስ ለዓመታት በዚህ ምርቷ ትታወቅ ነበር።

አስቤስቶ በግንባታ ኢንደስትሪ ላይ የተሰማሩ አካላት የሚጠቀሙበት ሲሆን በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ማዕድኑ ገዳይ የሆነ በሽታ ጋር የተያያዘ ነው።

አገራት ይህንን እንደ ካንሰር ያሉ ገዳይ በሽታዎች አምጪ የሆነውን ማዕድን ወደ አገራቸው እንዳይገባ ማገድ ከጀመሩ በኋላ የማዕድኑ ተፈላጊነት በዓለም ደረጃ ቀንሷል።

ካናዳ አስቤስቶ በአገሯ ጥቅም ላይ እንዳይውል ያገደችው በ2018 ነው።