ቁጣ የቀሰቀሰው የሕንድ ጌጣጌጥ ማስታወቂያ ተሰረዘ

የፎቶው ባለመብት, Tanishq
ታኒሽቅ የተባለው ዝነኛ የሕንድ ጌጣጌጥ አምራች ቁጣ የቀሰቀሰውን ማስታወቂያ ሰረዘ።
ማስታወቂያው የተለያየ ሃይማኖት የሚከተሉ ጥንዶችን የሚያሳይ ነበር። ቀኝ ዘመሞች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማስታወቂያውን በመኮነናቸው ድርጅቱ ሰርዞታል።
ማስታወቂያው ላይ የሂንዱ ሃይማኖት ተከታይ ሴት በባለቤቷ ሙስሊም ቤተሰቦች ስጦታ ሲበረከትላት ይታያል። ነፍሰ ጡር የሆነችው ሴት፤ ከመውለዷ በፊት ወዳጅ ዘመዶቿ ስጦታ የሚያበረክቱላት ቀን (ቤቢ ሻወር) ሲከበር በማስታወቂያው ይታያል።
ሙስሊም ወንዶች ሂንዱ ሴቶችን ወደ እስልምና እየለወጡ ነው ብለው የሚያምኑ አክራሪ ሂንዱዎች፤ ማስታወቂያውን አጥብቀው ተቃውመዋል።
ሕንድ ውስጥ የተለያየ ሃይማኖት ተከታዮች ጋብቻ ተቃውሞ ይገጥመዋል።
ወግ አጥባቂ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ጌጣጌጥ አምራቹ እንዲታገድ ጠይቀዋል። ትዊተር ላይ በርካቶች የተነጋገሩበት ቁጥር አንድ ጉዳይም ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩቲዮብ ላይ የተለቀቀው ማስወቂያ "የባሏ ቤተሰቦች ልክ እንደልጃቸው ይወዷታል። ሌላ ጊዜ የማያከብሩትን በዓል ለሷ ሲሉ አክብረዋል። ሁለት ሃይማኖቶች እና ባህሎች አንድ ላይ ሲጣመሩ ውብ ነው" የሚል መግለጫ ነበረው።
43 ሰከንድ የሆነው የጌጥ ማስታወቂያ፤ ከድርጅቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ተነስቷል።
ድርጅቱ ማስታወቂያውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያወጣው አስተያየት መቀበያ ሳጥኑን እንዲሁም ተመልካቾች መውደድ ወይም መጥላታቸውን የሚገልጹበት ቁልፍ እንዳይሠራ አድርጓል።
ኋላ ላይ ግን ማስታወቂያውን ሙሉ በሙሉ አስወግዷል።
ተቃዋሚ የምክር ቤት አባል ሳሺ ታሮር ማስታወቂያውን ደግፈው በትዊተር ገጻቸው አጋርተውታል።
"የሂንዱና የሙስሊም ጋብቻ እንዲህ የሚረብሻቸው ከሆነ የሂንዱዎችና የሙስሊሞች አንድነት ተምሳሌት የሆነችው ሕንድን ለምን አይቃወሙም?" ብለዋል።
አብዛኛው ሕንዳዊ ቤተሰብ ልጆቻቸው ተመሳሳይ ሃይማኖት ካለው ሰው ጋር ትዳር እንዲመሠርቱ ይፈልጋሉ። ከሃይማኖታቸው ውጪ ያለ ሰው በማግባታቸው ጥቃት የደረሰባቸው፣ በዘመዶቻቸው የተገደሉም አሉ።
አንድ የአገሪቱ ጥናት፤ የተለያየ ጎሳና ሃይማኖት ያላቸው ጥንዶች 5 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ያሳያል።
አንዳንዶች ከጎሳ ወይም ሃይማኖት ውጪ ያለ ጋብቻ በሕግ እንዲከለከል ይፈልጋሉ።
የጾታ እኩልነት አቀንቃኞች እንደሚሉት፤ ጫናው በሴቶች ላይ ይበረታል። አንዲት ሴት ከጎሳዋ ወይም ከሃይማኖቷ ውጪ ካገባች ቤተሰቧን እንዳዋረደች ተደርጎም ይታሰባል።
ከጎርጎሮሳውያኑ 2014 ወዲህ ሥልጣን ላይ ያለው የሂንዱ መንግሥት ጸረ ሙስሊም ንቅናቄዎችን በማበረታታቱ ይተቻል።
2018 ላይ ከሂንዱ ሴቶች ጋር የፍቅር ግንኙነት የመሠረቱ 102 ሙስሊሞች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር የሚያነሳሳ ጽሁፍ በፌስቡክ ተሰራጭቶ ነበር።
ከፍተኛ ቁጣ የቀሰቀሰው ይህ ጽሁፍ ከፌስቡክ ተወግዷል።












