ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ነጻነት፡ ከፈረንሳይ ‹‹ቅኝ ግዛት›› መላቀቅ የማትሻዋ ደሴት
ኒው ካሌዶኒያ ትባላለች፡፡ ደሴት ናት፡፡ በፓስፊክ ውቅያኖስ የምትገኝ ደሴት፡፡ የሕዝብ ብዛቷ 300ሺህ እየተጠጋ ነው፡፡
ፈረንሳይ በቅኝ ለመጀመርያ ጊዜ የያዘቻት በ1853 ዓ.ም (እንደነርሱ አቆጣጠር) ነበር፡፡ ይኸው እስከዛሬም ‹ቅኝ ግዛት› ተስማምቷት አለች፡፡
ትናንት ሕዝቧ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደርግ ነበር፡፡ ከፈረንሳይ ነጻ እንውጣ ወይስ በፈረንሳይ ሥር እንቀጥል የሚል፡፡
ድምጽ ከሰጠው ሕዝብ 53.26 ከመቶ የሚሆነው ፈረንሳይ ምን በደለችን፣ ተስማምታናለች፣ ሲል ድምጽ ሰጥቷል፡፡
ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገበው ሕዝብ ከፍተኛ የሚባለው 86 ከመቶው ፍላጎቱን በገለጸበት በዚህ ሕዝበ ውሳኔ ያቺ አገር ከ170 ዓመታት የፈረንሳይ ግዛት ቆይታ በኋላም ነጻነትን እንዳልናፈቀች ይፋ አድርጋለች፡፡
ይቺ አገር ባለፉት ሦስት ዓመት ብቻ ሁለት ጊዜ ተመሳሳይ ሕዝበ ውሳኔ አድርጋ ነዋሪዎቿ ከፈረንሳይ መለየት እንደማይፈልጉ በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የደሴቷ ነዋሪ በፈረንሳይ ሪፐብሊክ ላይ ላሳየው እምነት አመስግነዋል፡፡
በደሴቲቱ የአገሬው ነዋሪዎችና በሰፋሪዎች መካከል ግጭቶች ይከሰታሉ፡፡ ካናክ የሚባሉት የደሴቲቱ ቀደምት ነዋሪዎች ሲሆኑ ነጻ አገር መሆንን ይሻሉ፡፡ ሆኖም ግን ባለፉት 170 ዓመታት ውስጥ የወለዱና የተዋለዱ ሰፋሪዎች ይህ ፍላጎት የላቸውም፡፡
የደሴቲቱ 40 ከመቶ ነዋሪዎች ደግሞ የካናክስ ቀደምት የአገሬው ሕዝቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን አውሮጳዊያን ዝርያ ያላቸውና በደሴቲቱ ሰፋሪ ከነበሩ አውሮጳዊያን የተወለዱት በቁጥር የሕዝቡን አንድ ሦስተኛ ይዘዋል፡፡ ቀሪዎቹ የደሴቲቱ ነዋሪዎች ከፓሲፊክ ደሴት አገሮች የመጡና ክልሶች ናቸው፡፡
ኒው ካሌዶኒያ ደሴት ከፈረንሳይ ጋር በርካታ ስምምነቶችን አድርጋለች፡፡ በ1998 ያደረገችው የናውሚያ ስምምነት በተለይ ለደሴቲቱ ሰፊ ነጻነትን የሚያጎናጽፍ ነበር፡፡
የዚህ ስምምነት አንዱ አካል ኒው ካሊዶኒያ ሕዝቧ ባሻው ጊዜ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያደርግ ይፈቅዳል፡፡ ከዚህ በኋላ 3ኛው ሕዝበ ውሳኔ በ2022 ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኒው ካሌዶኒያ ለኤሌክትሮኒክስ ምርት ግብአት የሚሆነው ኒኬል ማዕድን ክምችት ያላት ደሴት ስትሆን ለፈረንሳይ በፖለቲካና በኢኮኖሚ በፓስፊክ እጅግ አስፈላጊ ግዛቷ ናት፡፡
ምንም እንኳ በብዛት እንደ ነጻ አገር ያህል ራስ ገዝ ብትሆንም በመከላከያ፣ በትምህርት እና በሌሎችም ዘርፎች የአቅኚዋን የፈረንሳይን ድጋፍ ትሻለች፡፡
ይቺ ደሴት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሚገኙ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ካልጀመሩ 17 አባል ግዛቶች ውስጥ የምትመደብ ሲሆን ከቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት ካልፈቀዱት ተርታ ትመደባለች፡፡
ኒው ካሌዶኒያ በአውስትራሊያና ፊጂ ደሴት መካከልል የምትገኝ ደሴት ናት፡፡
ፈረንሳይ ኒው ኬሎዲያንን በቅኝ የያዘቻት የዛሬ 170 ዓመት አካባቢ ነበር፡፡