ታንዛኒያ፡ በታንዛንያ 10 ተማሪዎች በእሳት ተቃጥለው የሞቱበት ትምህርት ቤት ባለቤት በቁጥጥር ስር ዋለ

የተቃጠለው ትምህርት ቤት

የፎቶው ባለመብት, Fedeco Radio

ታትሟል

የታንዛንያ ፖሊስ በሰሜን ምዕራብ ታንዛኒያ ካጌራ ክልል 10 ተማሪዎች በእሳት ተቃጥለው የሞቱበትን ትምህርት ቤት ባለቤት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ።

በቃጠሎው በርካቶች መጎዳታቸውም ተገልጿል።

ምርመራውን እየመሩ የሚገኙት ኢንስፔክተር ጄነራል ሳይመን ሲሮ ለቢቢሲ እንደገለፁት በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ላይ የተከሰተው እሳት ቃጠሎ መንስኤ ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው።

የምርመራቸው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንደሚያስረዳው ክፍሎቹ የተገነቡት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አለመሆኑን ነው።

እንደ ፖሊስ አዛዡ ከሆነ በመኝታ ክፍሎቹ ውስጥ የተዘረጉት የኤሌትሪክ መስመሮች ችግር ነበረባቸው። እንዲሁም በቃጠሎው የማደሪያ ክፍሎቹ ጣርያ ሲደረመስ ክፍሎቹ ሙሉ በሙሉ ተደርምሰዋል።

ይህ ደግሞ እንደ አዛዡ ከሆነ ክፍሎቹ የተገነቡት ከደረጃ በታች በሆኑ ብሎኬቶች ለመሆኑ ማሳያ ነው።

በሰሜን ምዕራብ ታንዛኒያ ካጌራ ክልል አስተዳደር የአካባቢውን ትምህርት ቢሮ ለዚህ አዳሪ ትምህርት ቤት እንዴት ፈቃድ እንደሰጠ ምርመራ እንዲደረግ ታዝዟል።

በሰሜን ምዕራብ ታንዛኒያ ካጌራ ክልል በአንድ አዳሪ ትምህርት ቤት ላይ እሳት ተነስቶ የሞት አደጋ ሲደርስ ሰባት ተማሪዎች ደግሞ ከባድ የመቁሰል አደጋ ገጥሟቸዋል።

በአደጋው በትንሹ 10 ተማሪዎች ሲሞቱ፣ ሌሎች ተማሪዎች ላይ ከባድና ቀላል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡

የትምህርት ቤቱ ማደርያ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ በእሳት የተበሉ ሲሆን የሟች ተማሪዎችም ሰውነት ለመለየት እስኪቸግር ድረስ በእሳት መበላቱ ብዙዎችን ያሳዘነ ሆኗል፡፡

የአዳጊዎቹን ማንነት ለመለየትና ሬሳ ለቤተሰብ ለመስጠት የዲኤንኤ ምርመራ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

ሰኞ ማለዳ አካባቢ በተማሪዎች መኖርያ ውስጥ ነበር እሳቱ የተቀሰቀሰው፡፡

ሟች አዳጊ ተማሪዎቹ ዕድሜያቸው ከ6 እስከ 10 ዓመት ቢሆን ነው፡፡

የክልሉ ኮሚሽነር ጋጉቲ ለሮይተርስ እንደተናገሩት በተማሪዎች ማደርያ 74 ተማሪዎች ነበሩ፡፡

እሳቱ እንደተነሳ አብዛኛዎቹ ታዳጊዎች ዘለው ማምለጥ ቢችሉም ሌሎች ግን አልተሳካላቸውም፡፡

ቢያሙንጉ ኢንግሊሽ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት የተነሳው በዚህ እሳት አደጋ መንስኤ በመጣራት ላይ ነው፡፡

ኢቴራ በተባለች በዚች ገጠር መንደር ሊቀመንበር የሆኑት ሙባራካ መሐመድ ‹‹ለመንደራችን ጨለማ ቀን ነው፡፡ ሐዘን ላይ ነን፤ ወላጆች ነዋሪዎች፣ የተማሪ ቤተሰቦች ከባድ ሐዘን ላይ ነን ብለዋል፡፡››

ባለፈው ሐምሌ በተመሳሳይ ዳሬሰላም በሚገኝ ኢላላ ኢስላሚክ ትምህርት ቤት በተነሳ እሳት አደጋ 3 አዳጊዎች መሞታቸው አይዘነጋም፡፡