ለጥቁሮች መብት የተዋደቀው 'ፈረንጁ' የማንዴላ ጠበቃ

ታትሟል

ጆርጅ ቢዞስ ይባላል። ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጣው የ2ኛው የዓለም ጦርነት አጋማሽ ላይ ነበር።

የትውልድ አገሩን ግሪክን ናዚዎች ወረሯት። እሱ ያኔ ገና 13 ዓመቱ ነበር።

ደቡብ አፍሪካ ሲደርስ እንግሊዝኛ ሁሉ አይችልም ነበር። ሆኖም እልኸኛ ነበር። በ1950 በሕግ ዲግሪውን ያዘ።

በዝነኛው የዊትወተርሳንድ ዩኒቨርስቲ ነው የተማረው። ለነገሩ ማንዴላም እዚሁ ነበር የተማሩት። እንዲያውም ማንዴላና ጆርጅ ቢዞስ የተገናኙት እዚህ ዩኒቨርስቲ ነበር።

በአፓርታይድ ጊዜ ለጥቁር ጠበቃ የሚቆም ነጭ ማግኘት ብርቅ ነበር። ቤዞስ ለተቸገሩ ጥቁሮች ብቻ ሳይሆን ለእውቅ የመብት ታጋዮች ጥብቅና በመቆም ማን ይቻለው።

በነገራችሁ ላይ ማንዴላ ወደ ጆሐንስበርግ እንደገቡ መጀመርያ ያደረጉት የጥብቅና ቢሮ መክፈት ነበር። በደል ለሚፈጸምባቸው ጥቁሮች በነጻ ጥብቅና ይቆሙ ነበር። ከጓደኞቻቸው ከነሲሱሉ እና ከነ ኦሊቨር ታምቦ ጋር።

ማንዴላ አገር በመክዳት ወንጀል 27 ዓመት ዘብጥያ እንዲወርዱ ሲፈረድባቸው ድንቅ ንግግር አድርገው ነበር።

በንግግራቸው ውስጥ ዝነኛዋን ሐረግ ያስገባው እሱ ነው። "if needs be" የምትለዋን ሐረግ። ‹‹አይደለም መታሰር…አስፈላጊ ከሆነም ለመሞት ዝግጁ ነኝ›› ብለው ነበር ማዲባ ያን ጊዜ፤ በፍርድ ቤት ቆመው።

ጆርጅ ቤዞስ ‹‹አስፈላጊ ከሆነም›› የምትለዋን ሐረግ ማስገባቱ በፍርድ ቤት ቋንቋ ትልቅ ትርጉም ነበረው። ምናልባትም ለማንዴላ ኋላ ላይ በድርድር መፈታትም አስተዋጽኦ አድርጎም ይሆናል።

ቤዞስ በዚህ አላቆመም።

ማንዴላ ሲፈቱና አዲስ ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ እሱ ከዚያ ከአዲሱ ሕገ መንግሥት መረቀቅ ጀርባ የነበረ ጎምቱ የሕግ ሰው ነበር።

አፓርታይድ በእርቅ ሲፈርስ በእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ውስጥ ቤተሰቦቻቸው በግፍ ለተገደሉባቸው ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን ቤዞስ በጥብቅና ቆሞላቸዋል።

በደቡብ አፍሪካ በ2012 ዓ.ም 34 የማዕድን ቁፋሮ ሰራተኞች በማሪካና የማዕድን ሥፍራ፣ በግፍ በፖሊስ ሲገደሉ ፍርድ ቤት ለሟች ቤተሰቦች ጠቀም ያለ የካሳ ገንዘብ እንዲከፈል እንዲፈርድ ያደረገውም ቤዞስ ነው። በዚህ ብዙዎች ስሙን ያወሱታል።

ቤዞስ ሲታወስ

ድምጹ ረጋ ያለና የሚማርክ ነው። ኩሩና መልከመልካም ነበር። ከከንፈሩ በላይ ወርቃማ ጢም ነበረው። ጆርጅ ቢዞስ ግርማ ሞገሱ የሚረሳ አልነበረም።

ማንዴላን ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው ፍርድ ቤት ጥብቅና የቆመላቸው ሁነኛ ሰው እሱ ነው። ከትናት በስቲያ በተወለደ በ92 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

ሥነ ሥርዓት ያለው፣ ሰው አክባሪ ነበር ይሉታል።

ጆርጅ ቢዞስ በነበረው ዝናና ክብር አፉን ዘግቶ የጡረታ ገንዘቡን እየበላ ተንደላቆ መኖር ይችል ነበር። ነገር ግን እንደዚያ አልነበረም።

በ80ና 90ኛ ዓመቱ እንኳ ዝም አላለም። ጥፋት ሲያይ ይናገራል። ጥቁሮች ሲበደሉ አያስችውም።

ቤዞስ የታላቁ ማንዴላን ሞት ተከትሎ በርሳቸው ኑዛዜ ዙርያ ቤተሰቡ ሲታመስ ሽምግልና ገብቶ ሰላም ያወረደ ሰው ነበር።

በአፓርታይድ ዘመን ከፈረንጆች ምግብ ቤት ገብቶ ተንደላቆ መመገብ እየቻለ ሆን ብሎ ከነ ማንዴላ ጋር ምግብ ቤት ይሄድ ነበር። የማይመጥኑት ምግብ ቤቶች፤ ለክብሩም ለቆዳ ቀለሙም፤ ቢያንስ ያን ጊዜ በነበረው አስተሳሰብ፣ እየገባ ይመገብ ነበር።

ማዲባ እና ጓደኞቹ እንደ ቤዞስ የሚያምኑት ነጭ ሰው አልነበረም። አግላይ የነበረውን አፓርታይድን ከጥቁሮች ጋር ጥሎ ለጡረታ ቢበቃም፣ ጥቁሮች በገዛ አገራቸው ዛሬም በድህነት ሲንከባለሉ ማየቱ ሁሌም የሚቆጠቁጠው ነገር ነበር።

የጥቁሮችን ፖለቲካዊ ነጻነት ቢመለከትም ኢኮኖሚያዊ ነጻነታቸውን ለማየት ግን ዕድሜው አልፈቀደም። ጆርጅ ቤዞስ።