አሜሪካ ከቻይና የተወሰኑ ምርቶች እንዳይገቡ ልታግድ ነው

ቻይና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አሜሪካ ከቻይና ግዛት ዢንጂያንግ የሚገቡ የተወሰኑ ምርቶች ወደ አገሯ እንዳይገቡ ልታግድ መሆኑ ተገለፀ።

ለአሜሪካ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈችው ምርቶቹ ሰዎች ያለፈቃዳቸው ጉልበታቸውን በመጠቀም የተመረቱ ናቸው የሚል ነው።

ምርቶቹን እንዳይገቡ የማድረግ እቅዱ የጥጥ እና ቲማቲም ምርቶችን የሚያካትት ሲሆን፤ እነዚህ ምርቶች ቻይና ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ሁለት ዋነኛ ምርቶች ናቸው።

የትራምፕ አስተዳደር የዢንጂያንግ የኡገር ሙስሊሞችን አያያዝ ተከትሎ በቻይና ላይ ጫና እያሳደረ ነው።

በቅርብ ዓመታትም ቻይና ገንጣዮችና ሽብርትኝነትን እንደ ችግር በመጥቀስም በዢንጂያንግ ያላትን የፀጥታ አካላት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምራለች።

በአንዳንዶች ግምት እስከ ሚሊየን የሚደርሱ ግለሰቦች በቀላል ጥፋቶች ያለ ምንም ክስ በካምፖች ውስጥ ታጉረው ይገኛሉ። ቻይና በበኩሏ ትምህርት የሚሰጥባቸው ካምፖች ናቸው እንጂ እስር ቤቶች አይደሉም ብላለች።

የአሜሪካ ጉምሩክና የድንበር ጥበቃ አሁን ላይ በግዳጅ የጉልበት ሥራ የሚመረቱ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ለማገድ የሚያስችል ሕግ እያዘጋጀ ነው።

ሕጉ ሕገ-ወጥ የሰዎችን ዝውውርን፣ የህፃናት የጉልበት ብዝበዛን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለመከላከል ያለመ ነው ተብሏል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች በዢንጂያንግ በግዳጅ የጉልበት ሥራ የሚመረቱ ሁሉንም ምርቶች ከግምት በማስገባት፤ በተገቢው መልኩ የተመረቱ መሆናቸውን የሚያሳይ ማረጋገጫ መጠየቅ የሚያስችል ሕግ አርቅቀው ነበር።

የጉምሩክና የድንበር ጥበቃ ኮሚሽነር ብሬንዳ ስሚዝ "ከዢንጂያንግ ከሚመጡ የጥጥ እና ቲማቲም ጋር በተያያዘ በምርት አቅርቦት ሂደት የግዳጅ ጉልበት የመጠቀም አጋጣሚዎች እንደሚኖሩ ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ ማስረጃ ባይኖረንም፤ ምክንያት ግን አለን " ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላትም ምርመራችንን እንቀጥላለን ብለዋል ኮሚሽነሯ።

ረቂቅ ሕጉ በአሜሪካ ነጋዴዎች፣ ልብስ አምራቾች እና የምግብ አቅራቢዎች ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል ተብሏል።

ቻይና የዓለማችንን 20 በመቶ ጥጥ ፍላጎት አቅራቢ ስትሆን አብዛኛው የሚመጣው ከዢንጂያንግ ግዛት ነው።

ግዛቷ የቻይና ፋብሪካዎች ግብዓት የሆኑ የፔትሮሊየም ኬሚካል እና ሌሎች ጥሬ እቃዎች ምንጭም ናት።