ትራምፕ ላይ በተመሰረተው የአስገድዶ መድፈር ክስ የፍትሕ መስሪያ ቤቱ ጣልቃ ሊገባ ነው

ጂን ካሮል፤ ዶናልድ ትራምፕ ደፍረውኛል ስትል ክስ መስርታለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጂን ካሮል፤ ዶናልድ ትራምፕ ደፍረውኛል ስትል ክስ መስርታለች
ታትሟል

የአሜሪካ ጀስቲስ ዲፓርትመንት ዶናልድ ትራምፕ መልበሻ ክፍል ውስጥ ደፍረውኛል በምትለው ሴት ላይ የሕግ አካሄድ ጉዳይ ላይ ውሳኔ አስተላልፏል።

በክሱ ሂደት ውስጥ ከእንግዲህ የአሜሪካ የፍትሕ መስሪያ ቤት የፕሬዝዳንቱን ጠበቃን ሚና ይወስዳል።

በመጽሔቶች አምደኛ የሆነችው ጂን ካሮል ትራምፕ ደፍረውኛል ያለችው በመንሐተን ኒው ዮርክ በ1990ዎቹ አካባቢ ነው።

ፕሬዝዳንቱ በበኩላቸው ሴትዮዋ "የኔ ምርጫ አይደለች" በሚል 'ማስጠሎ ስለሆነች ልደፍራት አልችልም' የሚል መንፍስ ያለው ንግግር መናገራቸው ብዙዎችን አበሳጭቶ ነበር። እሷም አዲስ የስም ማጥፋት ክስ መስርታባቸው እንደነበር ይታወሳል።

የትራምፕ ተቺዎች ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ ሆኖ እንዳይሰራ ዋይትሐውስ ጫና እየፈጠረበት ነው ብለው ይተቻሉ።

ይህን ያስባላቸው ታዲያ ጀስቲስ ዲፓርትመንቱ እንደ ፕሬዝዳንቱ ጠበቃ ሆኖ ይከራከርላቸው ተብሎ በመወሰኑ ነው።

እስካሁን ፕሬዝዳንቱ በክሱ ላይ ማርክ ካሶዊዝ በተባለ ጠበቃቸው ተወክለው ነበር ክሱን ሲከታተሉ የቆዩት። ፋይሉ የተከፈተውም በኒውዮርክ ስቴት ኮርት በኅዳር 2019 ነበር።

የትራምፕ ጠበቃ የሚሉት ይህ የስም ማጥፋት ክስ ሲመሰረትባቸው ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት አገራቸውን እያገለገሉ የነበረ በመሆኑ ተከላካይ ሆኖ ሊቀርብላቸው የሚገባው እኔ ጠበቃቸው ሳልሆን የመንግሥት ወኪል ነው መሆን ያለበት ይላል።

ፍርዱም መታየት ያለበት በክልል ደረጃ ሳይሆን በፌዴራል ፍርድ ቤት ነው።

ጉዳዩ ወደ ፌዴራል ሲሄድ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያለመከሰስ መብት ስለሚያገኙ ዶናልድ ትራምፕ በዚያ ነጻ ሊወጡ ይችላሉ የሚል ተሳቢ ተደርጓል።

በቴክሳስ ዩኒቨርስቲ የሕግ ፕሮፌሰር ስቲቭ ቭላዴክ ለሲኤንኤን እንደተናገሩት የጀስቲስ ዲፓርትመንቱ በዚህ ጉዳይ ላይ እጁን ያስገባል ተብሎ አይጠበቅም። ወይም የመሆን እድሉ አነስተኛ ነው።

ፕሮፌሰሩ እንደሚገምቱት ጉዳዩ ወደ ፌዴራል ካደገ ክሱ ያበቃለታል፤ ምክንያቱም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በስም ማጥፋት ሊከሰሱ የሚችሉበት እድል እየጠበበ ስለሚመጣ ነው።

ይህ ክሱን ወደ ፌዴራል የመግፋቱ ነገር የመጣው የግዛቱ ዳኛ ትራምፕ ያለመከሰስ መብት አለኝ ማለት እንደማይችሉ ከጠቆሙ በኋላ ነው።

ፕሬዝዳንቱ ለኅዳሩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከፍተኛ የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ናቸው።

ካሮል አሁን በአንድ መጽሔት ውስጥ አምደኛ ሆና ነው የምትሰራው።

ጉዳዩን ፌዴራል ዲፓርትመንት ይያዘው በሚለው ላይ በሰጠችው አስተያየት ፍርድ ቤት ማንኛችን ውሸታም እንደሆንን እንኳን እንዳይናገር ፕሬዝዳንቱ በስልጣናቸው ሁሉንም ነገር እየደፈጠጡ እንደሆነ ነው የሚገባኝ ብላለች።

የሷ የጠበቆች ቡድን እየጠየቀ ያለው ደግሞ ፕሬዝዳንቱ የዴኤንኤ ቅንጣት እንዲሰጡ ፍርድ ቤት እንዲያዝ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ያኔ ደፈሩኝ ባለች ጊዜ ከለበሰችው ልብስ ጋ በማዛመድ ድርጊቱ መፈጸም አለመፈጸሙ በቀላሉ መታወቅ ስለሚችል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ጀስቲስ ዲፓርትመንቱ እጁን ካስገባ አስደንጋጭ ነው የፍትሕ ሥርዓቱንም ያዛባል ብለዋል ጠበቃዋ ሮበርታ ካፕላን።

ትራምፕ የት ነው "የደፈሯት"?

ከሳሽ እንደምትለው በ1995 ትራምፕና እሷ በዝነኛው ቤርዶርፍ ጉድማን መደብር፣ ኒው ዮርክ ማንሐተን ነው የተገናኙት።

ያን ጊዜ ትራምፕ አፓርንቲስ ቴሌቪዥን ላይ የሚታዩ ዝነኛ ነበሩ። በሪልስቴትም ይታወቃሉ።

በመደብሩ ውስጥ ሁለቱም ግብይት ላይ እያሉ ‹‹ይህንን ቀሚስ ለአንዲት ሴት ጓደኛዬ ልገዛላት ነው ምን ታስቢያለሽ? ያምራል ወይ›› ብሎ ጠየቀኝ ትላለች። ‹‹ልኳ እንደሆነ እርግጠኛ ለመሆን በአንቺ ለክተሸ ባየው ደስ ይለኝ ነበር›› እንዳሏት ታስታውሳለች።

ፍቃደኝነቷን ገልጻ መልበሻ ክፍል ስትገባ ግን ትራምፕም ዘለው በመግባት ከግድግዳ ጋር አስጠግተው የመድፈር ሙከራ አድርገውብኛል ብላለች።

በመጨረሻ ታግዬ ገፍትሬው ወጣሁ ነው የምትለው።

ይህ በሚሆንበት ጊዜ እሷም ሆነች ትራምፕ 50 ዓመታቸው ነበር። ትራምፕ ያን ጊዜ ማርላ ማፕልስ አግብተው ባለትዳር ነበሩ።

ዶናልድ ትራምፐ ኮራል ቀጣፊ ዋሾ ናት፤ የምታወራውም ልቦለድ ነው። እሷን ልደፍር አልችልም፤ የኔ ምርጫም አይደለችም ብለው መናገራቸው ይታወሳል።