ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰሜን ኮሪያ በአውሎ ንፋስ ለደረሰው ጉዳት ባለስልጣናትን ተጠያቂ አደረገች
ሰሜን ኮሪያ ባሳለፍነው ረቡዕ ንፋስ የቀላቀለው ኃይለኛ ዝናብ ላደረሰው ጉዳት ባለስልጣናት ላይ እርምጃ እንደምትወስድ አሳወቀች።
የሰሜን ኮሪያ የሰራተኞች ፓርቲ ጋዜጣ በወደብ ከተማዋ ዎሳን በአውሎ ንፋሱ ለደረሰው ጉዳት የአከባቢውን ባለስልጣናት ተጠያቂ አድርጓል።
የአካባቢው ባለስልጣናት በቂ ዝግጅት ማድረግ ተስኗቸዋል ያለው ጋዜጣው፤ "ኃላፊነት የጎደለው አመለካከትም አለባቸው" ሲል የአካባቢው ባለስልጣናትን ተችቷል።
ጋዜጣው አውሎ ንፋሱ "በበርካቶች ላይ ጉዳት አስከትሏል" ይበል እንጂ ምን ያክል ሰዎች ላይ ምን አይነት ጉዳት እንደደረሰ ከመግለጽ ተቆጥቧል።
"ሰዎች ላይ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ በሆኑት ባለስልጣናት ላይ የአስተዳዳር እና የሕግ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተወስኗል" ሲል ጋዜጣው ጨምሮ አስነብቧል።
የቢቢሲዋ ኢሲያ ፓስፊክ አርታአይ ሴሊያ ሃተን የአካባቢው ባለስልጣናት አውሎ ንፋሱ ያደረሰውን ጉዳት ቀድመው መከላከል ይችሉ ነበር ወይ ብሎ ማጣራት አስቸጋሪ መሆኑን በማስታወስ፤ ግለሰቦቹ በፓርቲው ዒላማ ውስጥ ገብተው አልያም የሕዝቡን ቁጣ ለመቀነስ ታስቦ የተወሰደ እርምጃ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁማለች።
ቀደም ሲል በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጎርፍ ድልድዮችን ሲያፈራርስ አሳይቷል።
የሰሜን ኮሪያ ተራሮች እና የከፍታ ቦታዎች ከፍተኛ በሆነ መልኩ በደን ምንጠራ ስለተጎዱ ሰሜን ኮሪያ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ናት።