ሰሜን ኮሪያ ጃፓንን በእውነተኛ ሚሳዔል እንዳላጋይሽ ስትል አስፈራራቻት

ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤን 'ደደብ' እና 'ድንክ ፖለቲከኛ' ስትል ዘልፋለች።

ዘለፋው የመጣው ሺንዞ አቤ ሰሜን ኮሪያ ሐሙስ ዕለት በተከታታይ የባለስቲክ ሚሳዔል ሙከራ አድርጋለች ብለው ከወቀሱ በኋላ ነው።

ሰሜን ኮሪያ ግን እኔ ባለስቲክ ሚሳዔል አልተኮስኩም፤ ባይሆን ተለቅ ያለ የሮኬት ማስፈንጠሪያ እየሞከርኩ ነበር ስትል ወቀሳውን አስተባብላለች።

ቅዳሜ ዕለት የመንግሥት ልሳን የሆነው የሰሜን ኮሪያ ቴሌቪዥን ባስደመጠው ሃተታ 'ጃፓን ባለስቲክ ሚሳዔል እንዴት ያለ እንደሆነ ካላወቀች ምናልባትም በቅርቡ በባለስቲክ ሚከሳዔል አጋይተን እንሳያት ይሆናል ሲል ዛቻ አሰምቷል።

በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ምክረ-ሃሳብ መሠረት ሰሜን ኮሪያ የባለስቲክ ሚሳዔል ሙከራ ማካሄድ አትችልም።

ሰሜን ኮሪያ የጃፓን ወዳጅ ከሆነችው አሜሪካ ጋር በተደጋጋሚ ለንግግር መቀመጧም የተጣሉባት የተለያዩ ማዕቀቦች እንዲነሱላት በማለም ነው። ቢሆንም የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጁንግ-ኡን ግንኙነት የተጨበጠ ለውጥ አላመጣም።

ደቡብ ኮሪያ የሚገኙ ሰሜን ኮሪያ ሚሳዔል ስትተኩስ ተከታታለው የሚዘግቡ ታዛቢዎች ሐሙስ ዕለት ሰሜን ኮሪያ ሰማይ ላይ የታየውን 'ያልታወቀ መሣሪያ' ሲሉ ገልፀውታል።

ይህንን ሙከራ የተቃወሙት ጠ/ሚ አቤ «የሰሜን ኮሪያ የባለስቲክ ሚሳዔል ሙከራ ለሃገራችን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም አስጊ ነው» ሲሉ ተደምጠዋል።

የሰሜን ኮሪያው ጠቅላይ ገዥ ኪም ጁንግ-ኡን ሙከራውን ሲታዘቡ የሚያሳይ ፎቶ በሃገሪቱ ቴሌቪዥን ታይቷል። «አቶ አቤ በዓለም ብቸኛው ደደብ ሰው ናቸው ማለት ይቻላል። ባለስቲክ ሚሳዔልን ከሮኬት መለየት ካልቻለ በታሪክ ቂሉ ሰው ሳይሆን አይቀርም» ሲል ኬሲኤንኤ በዘገባው አስደምጧል።

ሰሜን ኮሪያ ግዙፍና ረዥም ርቀት ተጓዠ ባለስቲክ ሚሳዔል እየቀመረች ሳይሆን አይቀርም የሚል ጥርጣሬ ግን በብዙዎች ዘንድ አለ።