ለዓመታት በሐሰት ጥቁር ነኝ ያለችው ግለሰብ ከመምህርነቷ ታገደች

ታትሟል

አሜሪካ ውስጥ በርካታ ስራዎቿን ከአፍሪካውያን ዲያስፖራዎች ጋር ያገናኘችውና ጥቁር እንደሆነች ትናገር የነበረችው መምህሯ ጄሲካ ክሩግ ከመምህርነቷ እንደታገደች ታስተምርበት የነበረው የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል።

ጄሲካ ክሩግ በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ነበረች።

ጥቁር እንደሆነች ስትናገር የነበረችው ጄሲካ ትውልዷ ከካንሳስ ሲቲ መሆኑ እና ወላጆቿም አይሁዳዊያን እንደሆኑ አምናለች።

''ሕይወቴን በሙሉ ጥቁር ስለመሆኔ ስናገር ቆይቻለው፤ በእያንዳንዱ እስትንፋሴ ዋሽቻለው'' ስትል ጽፋለች።

የጄሲካ ባልደረቦችም ጥቁር አለመሆኗን ከገለጸች በኋላ መደናገጣቸውን ገልጸዋል።

ሐሙስ ዕለት ባሰፈረችው መልዕክት ጄሲካ ለዓመታት የሐሰት ማንነት መገንባቷን በመግለጽ ''ምንም መብት በሌላት ቦታ ላይ ተገኝቻለው'' ብላለች።

አክላም መጀመሪያ ላይ ከሰሜን አፍሪካ የመጣች ጥቁር እንደሆነች፣ በመቀጠል ደግሞ ጥቁር አሜሪካዊ እንደሆነች እንዲሁም ከካሪቢያን የመጣች ጥቁር እንደሆነች በተለያዩ አጋጣሚዎች መናገሯን ገልጻለች።

የአፍሪካ፣ ካሪቢያን እና ዲያስፖራ ታሪኮችን የምታስተምርበት የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ባወጣው መግለጫ ላይ ጄሲካ ክሩግ ከዚህ በኋላ በመምህርነት እንደማትቀጥልና በርካታ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሌሎችም በሁኔታው ማዘናቸውን ገልጿል።

ጄሲካ በጻፈችው መልዕክት ድርጊቷን ''የጭካኔ ትክክለኛ ማሳያ ነው'' በማለት የገለጸችው ሲሆን ''የሌሎችን ማንንት ሰርቄያለሁ፤ ጥቁር ያልሆኑ ሰዎች በጥቁሮች ላይ የሚደርሱባቸውን ጫና በመጥፎ ተጠቅሜያለሁ፤ በግል ሕይወቴ ሳይቀር እንደ ጥቁር ቀርቤያለው'' በማለት ገልጻዋለች።

ጄሲካ ይህንን ሁሉ ያደረግኩት "በልጅነቴ ባጋጠመኝ አሳዛኝ የአእምሮ ችግር ነው" ያለች ሲሆን ለድርጊቷ ግን ይሄ እንደ ምክንያት ሊቀርብላት እንደማይገባ ገልጻለች።

የጄሲካ ክሩግ የስራ ባልደረቦች ደግሞ በህብረት ባወጡት መግለጫ ከዩኒቨርሲቲ መምህርነቷ በገዛ ፍቃዷ ስራዋን እንድትለቅ ጠይቀዋል።

''በአሁኑ ሰዓት ትምህርታቸውን የሚከታተሉና የቀድሞ በርካታ ተማሪዎች፣ አስተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባልደረቦቿ በሙሉ እንደካደቻቸው ነው የሚያስቡት'' ብለዋል በመግለጫቸው።

ጄሲካ ክሩግ ምንም እንኳን ጥቁር አለመሆኗን ብታምንም ለምን ይህንን መረጃ ይፋ ለማድረግ እንደፈለገች ግን የገለጸችው ነገር የለም ተብሏል። ነገር ግን ታዋቂው የመድረክ ጸሃፊ ሃሪ ዚያድ የተባለ ግለሰብ መረጃውን ይፋ ያደረገችው ውሸቷ ስለተደረሰበት ነው ብሏል።