ከቻይና ጋር በመመሳጠር የተጠረጠሩት የቀድሞዋ የስዊድን አምባሳደር ችሎት ቀርበዋል

አና ሊንድስቴት

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

በስዊድን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንዲት የቀድሞ ዲፕሎማት የሃገር ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል ተከሰዋል፤ እሥርም ይጠብቃቸዋል።

አና ሊንድስቴት የተሰኙት ከሥልጣናቸው ውጭ በመሄድ ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር ተመሳጥረው አንድ ቻይና የተወለደ ስዊድናዊን ከእሥር ለማስቀለለቅ ሞክረዋል ተብሏል።

ቻይና፤ ጉዊ ሚንሃይ የተሰኘው ሆንግ ኮንግ ውስጥ መፅሐፍት በመሸጥ ይተዳደር የነበረው ግለሰብ መረጃ ለውጭ ሃገራት ይሰጣል በሚል አሥራዋለች።

አቃቤ ሕግ የቀድሞ አምባሳደር ስዊድን ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት አደጋ ላይ ጥለዋል ሲል ይከሳል። አልፎም ከስዊድን ሕግ ውጭ የሆነ ድርጊት ፈፅመዋል ሲል ክሱን አሰምቷል።

የዲፕሎማቷ ጠበቃ 'ደንበኛዬ ድርጊቱን አልፈፀሙም' ሲሉ ይሞግታሉ።

የተፈጠረው ምንድነው?

ባፈለው ዓመት የካቲት ሊንድስቴት ከቻይና አምባሳደርነታቸው እንዲነሱ ተደረገ። ይህ የሆነው ደግሞ ስዊድን በሚገኘው ሸራተን ሆቴል ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር ሕጋዊ ያልሆነ ውይይት አድርገዋል በሚል ነው። በውይይቱ ላይ የሚንሃይ ሴት ልጅና ከቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሁለት ነጋዴዎች ተገኝተዋል።

አባቷ እንዲፈታ ስትሞግት የነበረችው የሚንሃይ ልጅ ስብሰባው ላይ እንድትገኝ የተጋበዘችው በአምባሳደሯ አማካይነት እንደሆነ ታስረዳለች። ለሁለት ቀናት በቆየው ውይይት ላይ ከተሳተፉት ሁለት ነጋዴዎች መካከል አንዱ አባቷ ለጥቂት ዓመታት ታስሮ እንዲወጣ የሚያትት ስምምነት እንደትፈርምና ስለ አባቷ መቀስቀስ እንድታቆም እንደገፋፋት ትናገራለች።

አልፎም አምባሳደሯ ስምምነቱን ካልፈረመች ቻይና ስዊድንን ልትቀጣት እንደምትችል እንደነገሯት ታስረዳለች።

አምባሳደሯ እስካሁን ድረስ ስለ ክሱ በአደባባይ የተናገሩት ነገር የለም። ነገር ግን ከቻያናውያኑ ጋር ሊያደርጉ ስላሰቡት ውይይት ለሚመለከታቸው በኢሜል ማሳወቃቸውንና እንደ አምባሰደርነታቸው ይህ ሥልጣን እንዳላቸው ይናገራሉ።

አቃቤ ሕግ ከሁለቱ ነጋዴዎች መካከል አንዱ የቻይናን መንግሥት ይወክላል ቢልም አምባሳደሯ ሰዎቹ ከቻይና መንግሥት ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም ይላሉ።

የስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድፕሎማቷ ጉዳዩን እንዲተውት የሚያሳስብ ኢሜል ልክያለሁ ቢልም አምባሳደሯ እኔ ምንም ዓይነት የኢሜል መልዕክት አልደረሰኝም ይላሉ።

21 የስዊድን የቀድሞ አምባሳደሮች ድጋፋቸውን ለሊንድስቴት ሰጥተዋል። አምባሳደሯ ያደረጉት የሚጠበቅባቸውን ነው ይላሉ።

ጉዊ ሚንሃይ ማነው?

ሚንሃይ ሆንግ ኮንግ ውስጥ የመፃሕፍት መሸጫ መደብር ያለው ግለሰብ ነው። በግሪጎሪ አቆጣጠር 2015 ላይ ታይላንድ ወስጥ ለሽርሽር እንዳለ ደበዛው ጠፋ። ከዚያ በኋላ በቻይና ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርቦ 2003 ላይ ስለተፈጠረ ጠጥቶ የማሽከርከር ክስተት ሲናገር ታየ።

ሚንሃይ በጠፉ ሰሞን ሌሎች አራት መፅሐፍ ሻጮች ድበዛቸው ጠፍቶ ነበር። ባለመፃሕፍት ቤቶቹ የቻይና ባለሥልጣናትን ጉድ የሚያሰጣ መፅሐፍ አሳትመዋል ተብለው ይፈለጉ ነበር። ከቆይታ በኋላ በቻይና ፖሊሶች እጅ ሥር እንዳሉ ተረጋገጠ።

ሚንሃይ 2017 ላይ ተለቀቀ። ነገር ግን ከስዊድን ባለሥልጣናት ጋር ወደ ቤይጂንግ በባቡር እያቀና ሳለ በቁጥጥር ሥር ዋለ። ለውጭ ሃገራት መረጃ በማሰራጨት የሚል ክስ በቻይና መንግሥት ተመሠረተበት።