ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሮማኒያ 14 ሺህ በጎችን የጫነው መርከብ ተገለበጠ
ታትሟል
ከሮማኒያ ምስራቃዊ የባህር ዳርቻ ኮንስታንታ ከተማ ሚዲና ወደብ 14 ሺህ በጎችን ጭኖ የተነሳው መርከብ የተገለበጠው ትናንት ጠዋት ነበር።
የመርከቡ ሠራተኞች የነበሩት 22 ሶሪያዊያንን ከአደጋው መታደግ ተችሏል።
ፖሊስ፣ የነፍስ አድን ሰራተኞችንን እና የሮማኒያ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎችን ባሳተፈው ሰፊ የነፍስ አድን ስራ እስከ አሁን ከ 14 ሺህዎቹ በጎች መታደግ የተቻለው 32 ቱን ብቻ እንደሆነ ታውቋል።
"ትንሽ ቁጥር ያላቸውን በጎች ማትረፍ ችለናል እነሱንም ያገኘናቸው እየዋኙ ነው" ብለዋል የኮንስታንታ የድንገተኛ አደጋዎች እርዳታ አገልግሎት ቃል አቀባይ።
ትናንት ማምሻውን ያቆመው የነፍስ አድን ስራ ዳግም ዛሬ ጠዋት እንደሚጀመር ይጠበቃል።
መጀመሪያ ወደ ባህሩ ወድቆ የነበረና መጠነኛ ጉዳት የደረሰበት አንድ የመርከቡ ሰራተኛ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።
ከሮማኒያ በጎቹን ጭኖ ወደ ሳውዲ አረቢያ በማቅናት ላይ የነበረው መርከብ የመገልበጥ አደጋ መንስኤ ገና በመጣራት ላይ ነው።