ክሪስ፡ የዓለማችን ፀጉራሙ በግ በአውስትራሊያ ሞተ

ታትሟል

የዓለማችን ፀጉራሙ በግ ክሪስ በመባል ይታወቃል። የሜሪኖ ዝርያ ያለው ይህ በግ በአውስትራሊያ መሞቱ ተነግሯል። 'ሜሪኖ' የተባለው የበግ ዝርያ ያላቸው በጎች ለስላሳና ብዙ ፀጉር ስላላቸው ከሌሎች ዝርያዎች ይለያሉ።

ከአራት ዓመታት በፊት በካንቤራ አቅራቢያ በዱር የተገኘው ክሪስ፤ ስድስት ዓመታትን እንዳስቆጠረ በተገመተ ፀጉር በመሸፈኑ የዓለምን ትኩረት መሳብ ችሎ ነበር።

መጀመሪያ ላይ በጉን ለመታደግ ሲባል የተሸለተው ፀጉርም 41.1 ኪሎ ግራም ይመዝን ነበር። ይህም ኋላ ላይ የዓለምን ክብረ ወሰን መያዝ መቻሉ ተረጋግጧል።

በጊዜው የእንስሳት ደህንነት ባለሙያዎች በጉ የተሸከመው ፀጉር ከተለመደው የበጎች ፀጉር በአምስት እጥፍ የሚበልጥ በመሆኑ ለጤናው አደጋ እንዳለው አስጠንቅቀው ነበር።

ከዚያም በኋላ በብሔራዊ የፀጉር ሸላቾች ሻምፒዮን ኢያን ኢልኪንስ ፀጉሩ ተቆርጧል። ኢያን በ35 ዓመታት የሥራ ልምዱ እንዲህ አይነት ነገር አጋጥሞት እንደማያውቅም ተናግሯል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ አውስትራሊያዊያንም በጉን በጉዲፈቻ ለማሳደግ ፈቃዳቸውን አሳይተው ነበር። ለብሶት የነበረው የፀጉር ካፖርት በኋላ ላይ በአውስትራሊያ ብሔራዊ ሙዚም ለዕይታ ቀርቧል።

ይሁን እንጂ ማክሰኞ ዕለት በደቡብ ዌልስ እርሻ በእርጅና ምክንያት መሞቱን ተንከባካቢው አስታውቀዋል።

የክሪስን ሞት ተከትሎም 'ሊትል ኦክ ሳንክቸሪ' የተሰኘ ድርጅት "ይህንን ውብ፣ ብልህ እና ወዳጅ ልብ ያለው እንስሳ በማጣታችን የልብ ስብራት ደርሶብናል" ሲል ሐዘኑን ገልጿል።

የዐሥር ዓመት ዕድሜ እንደነበረው የተገመተው ክሪስ፤ ለሞሪኖ የበጎች ዝርያ አማካይ ነው የተባለውን ዕድሜ ኖሯል።

እንደ ተንከባካቢው ኬት ሉኬ ከሆነ፤ ክሪስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኝ የነበረ ሲሆን ሞቱ ድንገተኛ ነው ሲሉ ለካንቤራ ታይምስ ተናግረዋል።

የእንስሳት ተንከባካቢው ድርጅት አክሎም "ክሪስ በፀጉሩ ዝነኛ ቢሆንም ለድርጅቱ ሠራተኞች ግን ከዚያ በላይ ነበር" ብሏል።