ከአጋቾች ለማምለጥ በባቡር መጓዝ ብቸኛ አማራጭ የሆነባት ከተማ

ታትሟል

ማኒር አወል አዶ ናይጄሪያ፣ አቡጃ ውስጥ የሚኖር ነጋዴ ነው። ካዱና ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰቦቹን በየሳምንቱ የመጠየቅ ልማድ አለው።

በያዝነው ዓመት መባቻ ላይ እንደተለመደው ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ ወደ ካዱና ሲሄድ ያልጠበቀው ገጠመው። አቡጃን ከካዱና ጋር በሚያገናኘው መንገድ ላይ ታገተ። አጋቾቹ ለአምስት ቀን በቁጥጥር ሥር አውለውት የነበረው ማኒር፤ ነጻነቱን የገዛው በ1,300 ዶላር ነበር።

"አጋጣሚው መጥፎ ጠባሳ ጥሎብኝ አልፏል" ይላል።

ናይጄሪያን ያስጨነቁ፣ ያስጠበቡ አጋቾች ዳግመኛ እንዳያግቱት በመኪና መጓጓዝ አቁሟል። እሱ ብቻ ሳይሆን በርካታ ናይጄሪያውያን በአጋቾች እጅ ላለመውደቅ በባቡር መሄድ ይመርጣሉ።

ማኒር ልጅ ሳለ በፖሊዮ ሳቢያ ተሰቃይቷል። ከአጋቾቹ ሮጦ ማምለጥ ያልቻለውም ለዚህ ነው።

"ከታገትኩበት ጊዜ ወዲህ በመኪና መሄድ እፈራለሁ። ደህንነት የሚሰማኝ በባቡር ስጓዝ ነው" ይላል።

አቡጃ ውስጥ ኑሮ ውድ በመሆኑ፤ ብዙዎች አቡጃ እየሠሩ ካዱና መኖር ይመርጣሉ። ስለዚህም ከአቡጃ ካዱና እየተመላለሱ ሕይወትን ይገፋሉ።

ከአቡጃ ካዱና 150 ኪሎ ሜትር ነው። በመኪና መሄድ ከወጪ አንጻር የተሻለ ቢሆንም፤ ብዙ በመኪና ይሄዱ የነበሩ ግለሰቦች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ስለዚህም በርካቶች ትንፋሻቸውን ለማቆየት በባቡር ይጓዛሉ።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2016 ላይ ሥራ የጀመረው ባቡር፤ በቀን ከ5,000 በላይ ተጠቃሚዎች አሉት። ባቡሩ በታጠቁ የጸጥታ ኃይሎችም ይጠበቃል። ከአጋቾች ለማምለጥ ብቸኛ አማራጭ የሆነው ባቡር፤ በብዙዎች ተፈላጊ እንደመሆኑ በቀላሉ አይገኝም።

አንድ የመደበኛ ክፍል ካርኒ በአራት ዶላር፣ የቅንጡ ክፍል ካርኒ ደግሞ በስምንት ዶላር ይሸጣል። ካርኒ ለማግኘት የሚሰለፉት ሰዎች ስፍር ቁጥር የላቸውም። ተጓዦች ወንበር ባያገኙም የባቡሩ መጸዳጃ ቤት አካባቢ ቆመው ቢሆንም ይሄዳሉ።

በሌላ በኩል አንዳንድ ኃላፊዎች ካርኒ ደብቀው ከተመን በላይ በመሸጥ ይታማሉ።

አጋቾቹ ሀብታም ድሀ ሳይሉ በመንገዱ የሚያልፉ ሰዎችን ባጠቃላይ ኢላማ ያደርጋሉ። በመንገዱ ዳርቻ የሚገኘው ጥቅጥቅ ደን ውስጥ ተደብቀው ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ካዋሉ በኋላ ገንዘብ እዲከፈላቸው ያስገድዳሉ።

ከዚህ ቀደም ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ መክፈል ያልቻሉ ታጋቾችን ገድለዋል። በእገታ ከ20 እስከ 150,000 ዶላር ያገኛሉ።

የፖሊስ ኃላፊው አባ ኪየሪ አጋቾችን ለማስቆም ልዩ ኃይል መቋቋሙን ይገልጻሉ።