የዩኬ ሙዚቀኞች ሁለት ሜትር መራራቅ ያስቸግረናል እያሉ ነው

ታትሟል

በቫይረሱ ክፉኛ ተጎድተው ከነበሩ የአውሮፓ አገሮች አንዳንዶቹ እንቅስቃሴ ላይ ጥለው የነበረውን ገደብ እያላሉ ነው። የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ተግባራዊ ተደርገው የነበሩ እገዳዎች ቀስ በቀስ ቢነሱም ሁሉም ነገር ወደ ቀድሞ ገጽታው አልተመለሰም።

ሰዎች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ቢፈቀድም፤ አካላዊ ርቀት መጠበቅ አለባቸው። ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ቢቻልም ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች የአፍና አፍንጫ ጭምብል ማድረግ ግዴታ ነው።

አንዳንድ ሙያዎች ግን አካላዊ ርቀት ለመጠበቅ አይመቹም። ከነዚህ አንዱ ደግሞ ሙዚቃ ነው። በአንድ መድረክ ላይ ተሰባስቦ ሙዚቃ ለማቅረብ፤ አንድ ሙዚቀኛ ከሌለው ሁለት ሜትር ይራቅ ቢባል ብዙም አያስኬድም።

የዩናይትድ ኪንግደም ሙዚቀኞች ወደ ሥራ ገበታችን እንድንመለስ ሁለት ሜትር ተራራቁ የሚለው ሕግ ይላላልን ብለዋል።

የአገሪቱ የሙዚቀኞች ማኅበር ኃላፊ ሆራስ ትሩብሪጅ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በሽታው እንዳይሰራጭ ሙዚቀኞች አንዳቸው ከሌላቸው ፊት ሆነው ከመጫወት ይልቅ ጎን ለጎን መሆን ይችላሉ።

ሁለት ሜትር ተራራቁ ቢባል ግን ሙዚቀኞች ይቸገራሉ ብለዋል።

መንግሥት በበኩሉ ሙዚቀኞቹ “ብልሀት የተሞላ ፈጠራ” ካቀረቡ እንደሚቀበል አስታውቋል።

በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ቴአትር ቤቶችና መዝናኛዎች ተዘግታል። በርካታ የዩኬ ፌስቲቫሎችም ተሰርዘዋል።

የሙዚቀኞች ማኅበሩ፤ ከባህል፣ ሚዲያና ስፖርት ተቋም ጋር እየተነጋገረ ነው። የሙዚቃ መሰናዶዎች በሕዝብ አደባባዮች እንዲካሄዱ ይፈልጋሉ። ታዳሚዎች ገንዘብ እንዳይነኩም መላ እንዘይዳለን ብለዋል።

የማኅበሩ ኃላፊ እንደሚሉት፤ ሕጉ ቢላላ ቀጥታ የሙዚቃ ትርኢቶችን መጀመርም ይችላል።

የዓለም ጤና ድርጅት በሰዎች መካከል የአንድ ሜትር ርቀት እንዲኖር ቢመክርም፤ ዩኬ ሁለት ሜትር ተራራቁ ትላለች።

ኃላፊው ሆራስ እንደሚናገሩት እንደ ፐርከሽን ላሉ የሙዚቃ መሣሪያዎች አካላዊ ርቀት መጠበቅ አያስፈልግም። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግም ይቻላል።

በርካታ ሙዚቀኞች ኮሮናቫይረስ ከመሰራጨቱ በፊት በዓመት ወደ 20 ሺህ ዩሮ ነበር የሚያገኙት። “አሁን ከገቡበት ማቅ የሚያወጣቸው ነገር አይታየኝም” ብለዋል ኃላፊው።

የባህል፣ ሚዲያና ስፓርት ተቋም ቃል አቀባይ “ለዩኬ ሙዚቀኞች ፈታኝ ወቅት ነው። በተለያየ መንገድ የገንዘብ ድጋፍ እያደረግንላቸው ነው” ብለዋል።