እስራኤል የአል ጀዚራዋን ጋዜጠኛ ሆነ ብላ መግደሏን የፍልስጤም ዐቃቤ ሕግ ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የፍልስጤም ዐቃቤ ሕግ የአል ጀዚራ ጋዜጠኛ ሺሪን አቡ አቅላን ሆን ተብሎ ከእስራኤል ወታደር በተተኮሰባት ጥይት መገደሏን በምርመራዬ አረጋግጫለሁ አለ።
ጥናቱን ይፋ ያደረጉት የፍልስጤም ዋና ዓቃቤ ህግ "ተኩስ የነበረው ከወራሪው ወገን ሲሆን ይህም ለመግደል ተበሎ የተደረገ ነው" ብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ሪፖርቱን ውድቅ አድርጎ "ግልጽ ቅጥፈት" ሲል ገልጾታል።
የእስራኤል ጦር የራሱን ምርመራ በማድረግ ላይ ያለ ሲሆን አቡ አቅላን የገደሉት የፍልስጤም ታጣቂዎች ሊሆኑ ይችላሉ ብሏል።
የ51 ዓመቷ ፍልስጤማዊ-አሜሪካዊት ሺሪን አቡ አቅላን ዌስት ባንክ በሚገኘው ጄኒን የእስራኤል ጦር የሚያደርገውን ዘመቻ ስትዘግብ ነበር የተገደለችው። ይህም ሰፊ ቁጣ ቀስቅሷል።
የዓይን እማኞች ተኩሱ የተከፈተው በእስራኤል ወታደሮች ነው ቢሉም እስራኤል አስተባብላዋለች። ጋዜጠኛዋን የገደለው ጥይት የያዘችው ፍልስጤም ጥይቱን ጨምሮ የጋራ ምርመራ ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኗ የተኩሱን ምንጭ ማወቅ እንዳልተቻለም አስታውቋል።
እስራኤል ጥይቱን ተኩሶ ሊሆን ይችላል ያለችውን ወታደር መሳሪያ መለየት ብትችልም ጥይቱን ሳትመረመርም እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል አስታውቃለች።
በዌስት ባንክ ራማላህ ከተማ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የፍልስጤም ዓቃቤ ህግ አክራም አል-ካቲብ እንዳሉት ሺሪን አቡ አቅላን የገደለው ጥይት 5.56 ሚሊ ሜትር ሲሆን ይህም የኔቶ ኃይሎች ከሚጠቀሙት ዓይነት ጋር ተመሳሳይነት አለው ብለዋል።
የፍልስጤም ባለስልጣናት ጥይቱን ለእስራኤል የማይሰጡ መሆኑን እና ፎቶውም ይፋ እንደማይደረግ አስታውቀዋል። ከዚህ ቀደም የፍልስጤም ባለስልጣናት በእስራኤል መርማሪዎች ላይ እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።
"ፕሬስ" የሚል ጽሑፍ ያለው የጥይት መከላከያ ጃኬት እና የራስ መከላከያ (ሄልሜት) ለብሳ የነበረው አቡ አቅላን በጥይት የተመታችው የእስራኤል ኃይሎች እና የፍልስጤም ታጣቂዎች ተኩስ በሚለዋወጡበት አቅራቢያ በሚገኝ መንገድ ላይ ነው።
በፍልስጤማዊያን ምርመራ መሠረት ለመሸሽ በምትሞክረበት ወቅት የእስራኤል ወታደር በቀጥታ ወደ አቡ አቅላን መተኮሱን ያረጋግጣል ሲሉ ብለዋል የፍልስጤም መሪዎች።
ከሺሪን አቡ አቅላን አቅጣጫ የመልስ ተኩስም ይሁን የድንጋይ ውርወራ አለመኖሩን ገልጸው የጥይቱ አቅጣጫ ከእስራኤል ኃይሎች በኩል መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተመታችበት አቅራቢያ የነበረ ዛፍ በጥይት የተመታ ሲሆን ዒላማ የተደረገበት እና ተደጋጋሚ መሆኑ ተኳሹ የላይኛውን የሰውነት ክፍሏን ትኩረት አድርጎ ለመግደል በማሰብ መተኮሱን የፍልስጤም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አክራም አል-ካቲበ ገልጸዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ቤኒ ጋንትዝ የፍልስጤምን ምርመራ አጣጥለዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
የራሱን ጊዜያዊ ምርመራ ከሁለት ሳምንታት በፊት ይፋ ያደረገው የእስራኤል ጦር ተኩሱ "በስፋት ከነበረበት የፍልስጤም ታጣቂዎች" አቅጣጫ ወይንም አንድ ወታደር "ከአሸባሪዎች ወደ መኪናው በመተኮሳቸው" በሰጠው የተኩስ ምላሽ ሊሆን ይችላል ብሏል።
ፍልስጤማዊያን በእስራኤሎች ላይ የሚያደርሱትን ተደጋጋሚ ጥቃት ተከትሎ ወታደሮቹ ወደ ጄኒን ያቀኑት "ተጠርጣሪ አሸባሪዎችን" ለመቆጣጠር መሆኑን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
ሰኞ ዕለት የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጉዳዩ ወደ ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ማቅናቱን አስታውቀዋል። እስራኤል ፍርድ ቤቱን ባትቀበለውም አይሲሲ ለፍርድ ያልቀረቡ የጦር ወንጀለኛ ግለሰቦችን የመመርመር ስልጣን አለው።
ሺሪን አቡ አቅላን በቀጠናው ልምድ ያላት እና አንቱታን ያተረፈች ጋዜጠኛ ነበረች። ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታትም የእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭቶችን ለአል ጀዚራ አረብኛው ጣቢያ ስታስተላለፍ ቆይታለች።














