ፈረንሳይ እና ጀርመን ፑቱን ከዘሌንስኪ ጋር 'ቀጥተኛ' እና 'ወሳኝ' ድርድር እንዲያካሂዱ አሳሰቡ

የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የፈረንሳይ እና የጀርመን መሪዎችን ለ80 ደቂቃ ያህል በስልክ አነጋግረዋል።
ታትሟል

የፈረንሳይ እና የጀርመን መሪዎች፣ ከዜለንስኪ ጋር 'ቀጥተኛ' እና 'ወሳኝ' የሆነ ድርድር እንዲያደርጉ የሩሲያውን ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲንን ማሳሰባቸውን የጀርመን መራሔ መንግሥት ጽ/ቤት አስታወቀ።

መሪዎቹ ኢማኑኤል ማክሮን እና ኦላፍ ስኮልዝ ከፕሬዚደንት ፑቲን ጋር የ80 ደቂቃ የስልክ ንግግር አድርገዋል።

የመራሔ መንግሥቱ ጽ/ቤት እንዳለው መሪዎቹ በንግግራቸው አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግና ሩሲያ ወታደሮቿን ከዩክሬን እንድታስወጣ ገፋፍተዋል።

እንደ ክሬሚሊን ከሆነ የሩሲያ መሪ፣ ሞስኮ ከኪዬቭ ጋር እንደገና ንግግር ለመጀመር ፈቃደኛ መሆኗን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በፑቲን እና በዩክሬን አቻቸው ቮሎድሚር ዘሌንስኪ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ንግግር ሊኖር ይችል እንደሆነ አልጠቀሰም።

ቀደም ብሎ የዩክሬን ፕሬዚደንት ለውይይቱ ጉጉት እንደሌላቸው ገልጸው፣ ነገር ግን ግጭቱን ለማስቆም ውይይቱ አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው ነበር።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈፀመችበት እአአ የካቲት 24 ቀን ጀምሮ የሩሲያ እና የዩክሬን ልዑካን በርቀት እና በአካል በመገናኘት ለበርካታ ጊዜ ውይይት አድርገዋል።

ይህ ጥረት ግን ጦርነቱ እንዲቆም አላስቻለም።

ፈረንሳይ እና ጀርመን፣ ወደ ማሪፖል፣ አዞቭስታል የብረታ ብረት ፋብሪካ የጦር ምርኮኛ ተደርገው የተወሰዱ 2 ሺህ 500 የዩክሬን ተዋጊዎችን እንዲለቁም ፑቲንን አሳስበዋል።

ፋብሪካው የሚገኝበት ደቡባዊ የወደብ ከተማ፣ የሩሲያ ኃይሎች የማያቋርጥ የቦምብ ድብደባን ተቋቁሞ አሁን ግን ፈራርሶ የሚገኝ ሩሲያ የተቆጣጠረችው የመጨረሻ ይዞታ ነው።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የሞስኮ ባለሥልጣናት ፋብሪካውን ሲከላከሉ የነበሩ ተዋጊዎች መማረካቸውን ተናግረዋል።

ሩሲያ ቀደም ብሎ ከ900 በላይ ተዋጊዎች በሩሲያ በተያዘቸው ዶኔስክ በምትገኝ መንደር ኦሌኒቭካ ውስጥ ወደ ተከፈተው እስር ቤት እንደተዛወሩ አስታውቃለች።

ከባድ ጉዳት ያጋጠማቸው ጥቂት ወታደሮችም በዶኔስክ ኖቫዞቭስክ ከተማ ወደሚገኝ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጿል።

ዩክሬን እነዚህ ወታደሮቿ በእስረኞች ልውውጥ እንደሚለቀቁላት ተስፋ እንዳላት ብትገልጽም ሩሲያ ግን ይህንን አላረጋገጠችም።

አንዳንድ የሩሲያ ሕግ አውጭዎች ግን ተዋጊዎቹ ለፍርድ ሊቀርቡ አሊያም ሊገደሉ ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ።

የአዞቭስታል ብረታ ብረት ፋብሪካ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ዩክሬን የአዞቭስታል ብረታ ብረት ፋብሪካን የተከላከሉት ተዋጊዎቿ በእስረኞች ልውውጥ እንደሚለቀቁላት ተስፋ እንዳላት ብትገልጽም ሩሲያ ግን ይህንን አላረጋገጠችም።

የፈረንሳይ እና የጀርመን መሪዎች በስልክ ውይይታቸው ሩሲያ በዩክሬን የኦዴሳ ወደብ ላይ የጣለችውን እገዳ እንድታነሳና እህል ወደ ውጭ መላክ እንዲቻልም ፑቲንን ጠይቀዋል።

ክሬሚሊን፣ ፑቲን በዓለም ያጋጠመውን የምግብ ቀውስ ስጋትን ለማስወገድ አማራጮችን እንደሚመለከቱ የገለጸ ሲሆን "ምዕራባውያንም በሩሲያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ያንሱ" ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሩሲያ "ሌላ አለመረጋጋትን ያስከትላል" ስትል ፈረንሳይ እና ጀርመን ለዩክሬን የጦር መሣሪያ አቅርቦታቸውን እንዳይጨምሩ አስጠንቅቃለች።