ሲቲ በአስደናቂ ሁኔታ ዘግይቶ ባስቆጠራቸው ጎሎች የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ሆነ

ታትሟል

ድል የራቀው ይመስል ነበረው ማንችስተር ሲቲ የማታ የማታ አስቶንቪላን በማሸነፍ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በኢትሃድ ስታዲየም አንስቷል።

ማንችስተር ሲቲ ከተከታዩ ሊቨርፑል ያለው የአንድ ነጥብ ልዩነት ነበር።

የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን በአምስት ዓመት አራተኛውን የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ማሸነፍ ይበቃው ነበር። ሊቨርፑል በበኩሉ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የሲቲን ነጥብ መጣል መጠበቅ ነበረበት።

ሁለቱም ቡድኖች ግን ቀድሞ ጎል ገብቶባቸው ነበር።

ሊቨርፑል ወደ ጨዋታው ተመልሶ አቻ ሲሆን ሲቲ ሁለተኛ ጎል አስተናግዶ ውጥረቱን ከፍ አደረገው።

የማቲ ካሽ እና ፊሊፔ ኩቲንሆ ጎሎች ሲቲ የውድድር ዓመቱን ያለዋንጫ የሚያጠናቅቅ አስመስሎት ነበር። በተለይ የኩቲንሆ ጎል ዋንጫው ወደ ሊቨርፑል የሚያቀና አስመስሎት ነበር።

ኢትሃድ ስታዲዬም ጸጥታ ሲሰፍን አንፊልድ ደግሞ ሞቅ ብሎ ታይቷል።

ከሊቨርፑል ጋር የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ያልቻለው ስቴቨን ዤራርድ አስቶን ቪላን እየመራ ለቀድሞ ክለቡ ባለውለታ ለመሆን ከጫፍ ደርሶ ነበር።

ተቀይሮ የገባው ኢካይ ጉንዶጋን በ76ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል ሲቲ ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል። ሮድሪ ከሁለት ደቂቃ በኋላ አቻ የምታደርገዋን ጎል አስቆጥሯል።

ዘጠኝ ደቂቃዎች ሲቀሩት ዋንጫው በኢትሃድ መቆየቱን ያረጋገጠች ጎል ጉንዶጋን ማስቆጠር ችሏል።

የሲቲን ነጥብ መጣል ሲጠባበቅ የነበረው ሊቨርፑል ዎልቭስን በማሸነፍ የኢትሃዱን ቡድን ላይ ጫና መፍጠር ችሎ ነበር።

ከድሉ በኋላ ፔፕ ጋርዲዮላ በደስታ በእንባ ታጥበው ወደ መልበሻ ክፍል ሲገቡ ታይተዋል።

በዚህም በድራማ ከተሞሉ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የፍጻሜ ቀን ጨዋታዎች መካከል ለመሆን በቅቷል።

ሲቲ ያለውን የበላይነት ተደራጅቶ ሲጫወት በነበረው ቪላ ላይ በማሳየት ክብሩን አስጠብቋል።

የመሃል ዳኛው ማይክል ኦሊቨር የጨዋታውን መጠናቀቅ የሚያበስረውን ፊሽካ ሲያሰሙ ደጋፊዎች ሜዳውን ወረውታል።

በኢትሃድ እና አንፊልድ ጨዋታዎችን የታደሙ ደጋፊዎች ስሜታቸው ከፍ እና ዝቅ ሲል አምሽቷል።

ቼልሲ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ቶተንሃም አራተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን አረጋግጧል።

አርሴናል ከኤቨርተን ጋር ያደረገውን ጨዋታ 5 ለ 1 ቢያሸንፍም አምስተኛ ሆኖ ለማጠናቀቅ ተገዷል። በዚህም የዩሮፓ ሊግ ተሳታፊ መሆኑም ተረጋግጧል።

በፓላስ 1 ለ 0 የተሸነፈው ማንችስተር ዩናይትድ ስድስተኛ በመሆን አጠናቋል።

ዌስት ሃም በብራይተን መሸነፉን ተከትሎ ነው ዩናይትድ የዩሮፓ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን የቻለው።

ዌስት ሃም የኮንፈረንስ ሊግ ተሳታፊ ይሆናል።

ኖርዊች እና ዋትፎርድን ተከትሎ የሚወርደውን ሦስተኛ ቡድን ለማወቅ እስከ መጨረሻው ጨዋታ ድረስ መጠበቅ ግድ ሆኖ ቆይቷል።

በኒው ካስል 2 ለ 1 የተሸነፈው በርንሌይ ከጨዋታው መጀመር በፊት ከወራጅ ቀጠና ውጭ ነበር።

18ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ሊድስ ከሜዳው ውጭ ብሬንትፎርድን 2 ለ 1 በማሸነፍ በሊጉ ለመቆየት ችሏል።

በዚህም በርንሌይ ሦስተኛው ወራጅ ቡድን መሆኑ ተረጋግጧል።

ሌላው ከፍተኛ ፉክክር የነበረበት የከፍተኛ ጎል አግቢነት ክብር ነበር።

ሞሃመድ ሳላህ እና ሰን ሁንግ-ሚን በ23 ጎሎች የወርቅ ጫማውን ክብር ተጋርተዋል።

የቀጣዩ ዓመት የሊጉ ውድድር ሐምሌ መጨረሻ ላይ ይጀመራል።