ማን ዋንጫውን ያነሳል? ማንስ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን ይሰናበታል?

ጀርገን ክሎፕና ጋርዲዮላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሊቨርፑል ወይስ ማንቸስተር ሲቲ? ቶተንሃም ከተቀናቃኙ አርሰናል በልጦ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ መሆን ይችል ይሆን? ፕሪሚዬር ሊጉን ማን ይሰናበታል? ሊድስ ወይስ በርንሊ?

ዛሬ ሰንበት በሚደረገው የመጨረሻው ዙር የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ፍልሚያ ምላሽ የሚያገኙ ጥያቄዎች ናቸው።

በፈረንጆቹ አቆጣጠር የ2021/22 የውድድር ዘመን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቋጫል።

በ10 ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ማን እንደሚያነሳ አሊያም ወራጅ ማን እንደሆነ ሳይለይ የሚደረግ የመጨረሻ ቀን ፍልሚያ ነው።

ሲቲ ዋንጫው በእጁ ነው

ማንቸስተር ሲቲዎች ከሊቨርፑል በአንድ ነጥብ ከፍ ብለው ሰንጠረዡን ይመራሉ።

ሲቲ ባለፈው ሳምንት ከዌስትሃም ገጥሞ ነጥብ ሲጥል ሊቨርፑል ደግሞ ሳውዝሃምፕተንን በመርታት የሲቲን ኮቴ መከተል ችሏል።

ብዙዎች ሲቲ ከአስተን ቪላ ያለበትን የዛሬውን ጨዋታ በመርታት ዋንጫውን ያነሳል የሚል ግምት አላቸው።

በፕሪሚዬር ሊጉ ታሪክ ደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ ያለ ክለብ በመጨረሻው ቀን ተረትቶ አያውቅም።

ነገር ግን ይህ ብቻ ሳይሆን የሲቲ ወቅታዊ አቋምም ነው ግምቱን ወደ ኤቲሃድ ስታድዬም እንዲያደላ የሚያደርገው።

ማንቸስተር ሲቲ በያዝነው የውድድር ዘመን ካደረጋቸው 37 ጨዋታዎች 28 ፍልሚያዎችን በድል ማገባደድ ችሏል።

አሠልጣኝ ፔፔ ጉዋርዲዮላ ከአስተን ቪላ የሚገጥሙት ማሸንፍና ማሸነፍ ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ አስበው ነው።

ፔፕ ዘንድሮ ዋንጫ ካነሱ በስድስት ዓመት አራተኛው መሆኑ ነው።

ሲቲ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሌሎች ውድድሮች ብዙም ውጤታም አልሆነም።

ለኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜ ለማለፍ በነበረው ፍልሚያ በሊቨርፑል ተረትቶ ሲወድቅ በቻምፒዮንስ ሊጉም እንዲሁም ወደ ፍፃሜ የሚያደርገው ጉዞ በሪያል ማድሪድ አስደናቂ ብቃት ከሽፏል።

ሲቲ የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ አነሳ ማለት ዩርገን ክሎፕ አራት ዋንጫዎችን በማንሳት ታሪክ ሊፅፉ የዋጡት ምራቅ ከንቱ ሆነ ማለት ነው።

ሊቨርፑል የካራባዎና ኤፍ ኤ ዋንጫዎችን አንስቷል። የፕሪሚዬር ሊጉ ዛሬ ይለያል። ቻምፒዬንስ ሊግ ደግሞ በቅርብ ቀናት።

ቀያዮቹ ማድረግ የሚችሉ ነገር ቢኖር ዎልቭስን ረትትወ አስተን ቪላ ሲቲን ነጥብ እንዲያስጥል በተስፋ መጠበቅ ብቻ ነው።

ሁለቱ ተፎካካሪ ክለቦች ሲቲና ሊቨርፑል ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ጨርሰዋል።

የሰሜን ለንደን ትንቅንቅ

ስፐርስ ባለፈው እሑድ ከበርንሊ ጋር የነበራቸውን አልህ አስጨራሽ ጨዋታ መርታታቸው አርሰናል ደግሞ ሰኞ ምሽት በኒውካስትል መሸነፉ፤ ቶተንሃም የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ እንዲሆን ተስፋ የሰጠ ነው።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከለንደን ተቀናቃኙ አርሰናል በሁለት ነጥብ ፈቀቅ ብሎ ተቀምጧል።

ዛሬ ከፕሪሚዬር ሊጉ መውረዱን ካረጋገጠው ኖርዊች ጋር የሚፋለመው የአንቶኒዮ ኮንቴ ቡድን አቻ እንኳ ቢወጣ አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቁን ያረጋግጣል።

አርሰናል ግን ጨዋታውን ማሸነፍ ብቻ ነው የቻምፒዮን ሊግ ተሳታፊ መሆኑን የሚያስረግጥለት።

ሌላው የአህጉር ውድድር ጉዳይ ማን የአውሮፓ ሊግ ማንስ የኮንፈረንስ ሊግ ተሳታፊ ይሆናል የሚለው ነው።

የሚያስከፋ የውድድር ዘመን ያሳለፉት ማንቸስተር ዩናይትዶች ከዌስትሃም በሁለት ነጥብ ከፍ እንዳሉ ወደ ክሪስታል ፓላስ ሜዳ አቅንተው የመጨረሻ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ዩናይትድ ማሸነፍ ብቻ ነው የሚያዋጣው። አሊያ የአውሮፓ ሊግ ዕድሉን ለዌስትሃም አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል።

በዴቪድ ሞዬስ የሚመራው ዌስትሃም በዚህ ዓመት ለግማሽ ፍፃሜ ደርሰው የተሸነፉበትን አህጉራዊ ውድድር ድጋሚ ለመጎብኘት ከብራይተን ይፋለማሉ።

ከዚህ በታች ያሉ ክለቦች ያላቸውን የደረጃ ሰንጠረዥ በአንድ ካሻሻሉ ተጨማሪ 3 ሚሊዮን ዩሮ ያገኛሉ ማለት ነው።

ለምሳሌ አስተን ቪላ በመጨረሻው ቀን ጨዋታ ከ14ኛ ወደ 10 ማደግ ቢችል 12 ሚሊዮን ዩሮ ያገኛል።

ሊድስ ወይስ በርንሊ?

ባሳለፍነው ሳምንት ኤቨርተን ከክሪስታል ፓላስ ሲፋለም በጨዋታው አጋማሽ የወራጅ ቀጣና ውስጥ ነበር።

ነገር ግን ኤቨርተን ሁለት ለምንም ከመመራት ተነስቶ ጨዋታውን ሶስት ለሁለት በመርታት ደጋፊዎችን በፌሽታ አስፈንጥዟል።

ይህ ማለት ሊድስና በርንሊ ብቻ ናቸው ዋትፈርድና ኖርዊችን ለመቀላቀል የሚፋለሙት ማለት ነው።

ሁለት ክለቦች እኩል 35 ነጥብ ቢይዙም በጎል መጠን ግን በርንሊ በልጦ ከላይ ተቀምጧል።

በርንሊ በሜዳው ከኒውካስትል ሊድስ ደግሞ ከሜዳው ውጭ ከብሬንተፈርድ ይፋለማሉ።