ኩሽና ውስጥ የቆየ የቻይና ጥንታዊ የአበባ ማስቀመጫ 78 ሚሊዮን ብር ተሸጠ

ባለሰማያዊ ቀለሙ የአበባ ማስቀመጫ

የፎቶው ባለመብት, Dreweatts

የምስሉ መግለጫ, ባለሰማያዊ ቀለሙ የአበባ ማስቀመጫ
ታትሟል

"ዓይነቱን ልዩ የሆነ" የ18ኛው ክፍለ ዘመን የቻይና የአበባ ማስቀመጫ በ1.5 ሚሊዮን ዩሮ ተሸጠ።

ይህ የአበባ ማስቀመጫ በ1980ዎቹ በጥቂት መቶ ፓውንዶች ተሸምቶ ኩሽና ውስጥ ተቀምጦ ቆይቷል።

60 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው ባለሰማያዊ ቀለሙ አነስ ያለው ማሰሮ መሳዩ የአበባ ማስቀመጫ፤ በኪያንሎንግ ንጉሣዊ አገዛዝ ዘመን የተሠራ ነው።

ማሰሮው በለሊት ወፍና "ክሬን" በተባለች አንገተ መለሎ ወፍ ምስል በብርና በወርቃማ ቀለም ያጌጠ ነው።

ይህ የአበባ ማስቀመጫ አንድ የቀዶ ህክምና ባለሙያ ገዝቶት ለልጁ በስጦታ ያስተላለፈው ሆኖ ተገኝቷል።

ጥንታዊው ቁስ ቢያንስ 100 ሺህ ቢበዛ ደግሞ 150 ሺህ ዩሮ ያወጣል ተብሎ ተገምቶ ነበር።

ነገር ግን ጨረታው ላይ የተገኙ የጥንታዊ ቁስ ሙያተኞች የማሰሮውን ታሪክ አጥንተው ሲደርሱበት ዋጋው ጣራ ነካ።

የአበባ ማስቀመጫው በስልክ በተደረገ ጨረታ ለአንድ ግለሰብ በጠቅላላ ዋጋ በ1.5 ሚሊዮን ዩሮ [78 ሚሊዮን ብር] ተሽጧል።

አጫራቹ ኩባንያ በርካታ ተጫራቾች ከቻይና፣ ከአሜሪካና ከዩናይትድ ኪንግደም ዕቃውን ለመግዛት እንደተሟገቱ አስታውቋል።

ማሰሮው ላይ የተሣሉት አእዋፋት ረዥም ዕድሜና ብልፅግናን የሚያሳዩ ናቸው ተብሏል።

የአበባ ማስቀመጫው ከ1736-1795 የነበረውን የኪያንሎንግ ንጉሣዊ አገዛዝ ምልክት አስፍሯል።

አጫራቹ ኩባንያ መሰል ማሰሮ በዚህ ዘመን መገኘቱ በጣም የሚያስገርም ነው ብሏል።

አክሎም እንዲህ ዓይነት የአበባ ማስቀመጫ ከዚያ ዘመን በኋላ ስለመሠራቱ የሚያሳይ መረጃ እንደሌለ ገልጧል።

የአበባ ማስቀመጫው ባለቤት ማሰሮው ይህን ያህል ዋጋ ያወጣል ብሎ እንዳልገመተ ተናግሯል።