ቶተነሃም ከአርሰናል፡ በጉጉት የሚጠበቃው የሰሜን ለንደን ደርቢ

አርሰናል ከቶተነሃም

የፎቶው ባለመብት, Clive Rose

ታትሟል

ሊጠናቀቅ የሁለት ሳምንት የጨዋታ ዕድሜ የቀረበው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ አንድ ወሳኝ ጨዋታን ያስተናግዳል።

ይህ ጨዋታ በቀጣይ እንግሊዝን ወክለው በቻምፒየንስ ሊግ የሚሳተፉ ቡድኖችን ሊለይ ይችላል።

በጉጉት የሚጠበቀው የቶተነሃም እና አርሰናል የሰሜን ለንደን ደርቢ 3፡45 ሲል ይጀምራል።

ባላንጣ የሆኑት ሁለቱ ክለቦች የሞት ሽረት ትግል ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የዚህ ጨዋታ ውጤት የሁለቱንም ቡድን የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎን መወሰን ይችላል።

መድፈኞቹ፤ በቶተነሃም ላይ ድል ከተቀናጁ ከ5 ዓመታት በኋላ ወደ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር በመመለስ ሕልማቸውን ያሳካሉ።

የአርሰናል አሰልጠኝ ሚኬል አርቴታ፤ የጨዋታውን ወሳኝነት ለተጫዋቾቼ ማስታወስ አያስፈልገኝም ይላሉ።

"መልዕክቱ ግልጽ ነው። ካሸነፍናቸው በቀጣይ የውድድር ዘመን ቻምፒየንስ ሊግ ውስጥ ነን። ተጨዋቾቹን ለማነቃቃት ከዚህ በላይ ምንም መናገር አያስልግም።"

በ4 ነጥቦች በአርሰናል ተበልጦ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶተነሃም፤ በቀላሉ እጅ አይሰጥም። እንዲያውም የተሻለ የማሸነፍ ዕድል እንዳለው ተገምቷል።

አንቶኒዮ ኮንቴ ግን ይህን ያውቃሉ፤ ከሰሜን ለንደን ተፎካካሪያቸው አርሰናል ብርቱ ትግል እንደሚጠብቃቸው።

"ከአርሰናል ጋር ያለው ፉክክር በጣም ከፍተኛ ነው። ይህ ደግሞ ልዩ ደርቢ ነው። የተቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን። ምክንያቱም ይህ ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ልዩነት ያመጣል።"

ይህን ጨዋታ አርሰናል የሚያሸንፍ ከሆነ፤ ማንችስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል እና ቼልሲን ተከትሎ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊነቱን ያረጋግጣል።